Fana: At a Speed of Life!

የእርሻ መሬት ወስደው ወደ ሥራ በማይገቡ ባለሃብቶች ላይ እርምጃ ይወሰዳል- የቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ጋምቤላ ክልሎች

አዲስ አበባ፣ የካቲት 21፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ)ሰፋፊ የእርሻ መሬት ወስደው ወደ ሥራ በማይገቡ ባለሃብቶች ላይ እርምጃ እንደሚወስዱ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ጋምቤላ ክልሎች አሳሰቡ፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ባቡከር ካሊፋ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት÷በክልሉ ከ900 በላይ ባለሀብቶች በሠፋፊ እርሻ ላይ ለመሠማራት ቦታ ቢወሥዱም ወደ ሥራ የገቡት ግን ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው።

ለዚህም በክልሉ የነበረውን የፀጥታ ችግር እንደ ምክንያት የጠቀሱት ኃላፊው አሁን ላይ በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች ሠላም የተረጋገጠ በመሆኑ ሁሉም አካል ወደ ሥራ እንዲገባ ነው ያሳሰቡት።

የጋምቤላ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ሀላፊ አቶ አጃክ ኡቻን በበኩላቸው ÷ክልሉ ካለው ፀጋ አንፃር እስካሁን ምንም እንዳልተጠቀመ ገልጸው አሁን ላይ የክልሉ መንግሥት ሠፋፊ የእርሻ ቦታዎችን ወደ ሥራ ለማስገባት እየሰራ እንደሆነ ተናግረዋል።

በክልሉ ለእርሻ ልማት ሥራ ቦታ ወስደው ያላለሙ ባለሃብቶች ወደ ሥራ መግባት እንዳለባቸው ነው ኃላፊው አፅንኦት የሰጡት።

በሰሎሞን ይታየው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.