የሀገር ውስጥ ዜና

በአዲስ አበባ ማምሻውን በደረሱ ሶስት የእሳት አደጋዎች በንብረት ላይ ከባድ ጉዳት ደረሰ

By Mekoya Hailemariam

March 01, 2023

አዲስ አበባ፣ የካቲት 22፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ትላንት ማምሻውን በደረሱ ሶስት የእሳት አደጋዎች በንብረት ላይ ከባድ ጉዳት ደረሰ።

ትናንት ምሽት 11:26 በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 አደይ አበባ አካባቢ ባጋጠመ የእሳት አደጋ በሁለት ሆቴሎችና በአንድ ፔንሲዮን ላይ ጉዳት ደርሷል።

ምሽት 12:20 ሰዓት ንፋሰ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ  ወረዳ  አንድ ደግሞ በአንድ ባጃጅ ላይ በደረሰ የእሳት አደጋ ባጃጇ ሙሉ በሙሉ ተቃጥላለች።

ምሽት 3:05 ሰዓት ላይ በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 ዘነበ ወርቅ ባጃጅ ተራ የተለያዩ የንግድ አገልግሎት የሚሰጥባቸው 6 የንግድ ቤቶች ተቃጥለዋል።

የእሳት አደጋዉን ለመቆጣጠር 13 የአደጋ መቆጣጠር ተሽከርካሪዎች፣ ሁለት አምቡላንስ  እና 78 የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች የተሰማሩ ሲሆን፥ የእሳት አደጋዎቹ ተዛምተው  የከፋ ጉዳት እንይደርስ ማድረግ ተችሏል።

ሶስቱንም የእሳት አደጋዎች ለመቆጣጠር አምስት ሰዓት የፈጀ ሲሆን፥  በደረሱት የእሳት አደጋዎች በሰው ላይ የደረሰ ጉዳት አለመኖሩን የአዲስ አበባ እሳትና ስጋት አመራር ኮሚሽን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት አስታውቋል።