Fana: At a Speed of Life!

በኦሮሚያ ክልል ለመንገድ ጥገና ከ3 ቢሊየን ብር በላይ ለመሰብሰብ ታቅዷል

አዲስ አበባ፣ የካቲት 22፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኦሮሚያ ክልል መንገዶች እና ሎጅስቲክስ ቢሮ በሦስት ዓመታት ውስጥ ከመንግሥት፣ ከሕዝብ እና ከተለያዩ ስጦታዎች ከ3 ቢሊየን ብር በላይ በመሰብሰብ 20 ሺህ 242 ኪሎ ሜትር መንገድ ለመጠገን ማቀዱን ገለጸ፡፡

በመንገድ ጥገና ዘርፍ የመንገድ ደኅንነትን በማስጠበቅ የህብረተሰቡን ፍላጎት ለማሟላት የኦሮሚያ መንገዶች ፈንድ አዋጅ ቁጥር 224/2012፣ ደንብ 223/2013 እና መመሪያ 01/2014 በተያዘው በጀት ዓመት ወደ ሥራ መግባቱን ቢሮው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ገልጿል፡፡

የፈንዱ ዓላማም በፌደራል መንግሥት የመንገድ ፈንድ ከሚጠገኑት ውጭ ያሉ የክልሉን የጠጠር መንገዶች ለመጠገን፣ ለማሻሻል፣ ለማስተዳደር እና ደኅንነታቸውን ለማረጋገጥ የሚያስፈልጉ ወጪዎችን መሸፈን ነው ተብሏል፡፡

የቢሮው ምክትል እና የመንገድ አስተዳደር ዘርፍ ኃላፊ ኢንጅነር ታመነ ታደሰ እንዳሉት፥ መንገዶችን በመጠገን እና በማሻሻል ለረጅም ጊዜ እንዲያገለግሉ የማድረግ ሥራው በመንግስት አቅም ብቻ የሚፈጸም አይደለም፡፡

በመሆኑም የመንገድ ፈንድ በማቋቋም ለጥገናዎቹ የሚውል ቋሚ የፋይናንስ ምንጭ እንዲኖር ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ የኦሮሚያ መንገዶች ፈንድ ወደ ሥራ ገብቷል ነው ያሉት፡፡

በሁሉ አቀፍ የገጠር ተደራሽ መንገድ ፕሮግራም (ዩራፕ) ለተሠሩ መንገዶች የተያዘ የጥገና በጀት አለመኖር እና መንገዶቹ የሚሰጡት አገልግሎት ከታሰበው በላይ ከፍተኛ የትራፊክ ፍሰት ያለበት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

መንገዶቹ ለረጅም ዓመታት በማገልገላቸው አሁን ተጎድተዋል ያሉት የቢሮው ምክትል ኃላፊ÷ መንገዶቹ የተሳለጠ አገልግሎት እንዲሰጡ ጥገና እንዲደረግላቸው የሕዝብ ፍላጎት መጨመሩን ጠቁመዋል፡፡

ከክልሉ ሕዝብ እና ባለድርሻ አካላት ቋሚ ገቢ በመሰብሰብ በዩራፕ የተሠሩ መንገዶችን ለመጠገን በታሰበው መሰረትም÷ በ2015 ዓ.ም በክልሉ ከሚገኙ ዞኖች ከ498 ሚሊየን 290 ሺህ ብር በላይ ለመሰብሰብ ታቅዷል ብለዋል፡፡

በዚህም 4 ሺህ 334 ኪሎ ሜትር መንገድ ለመጠገን እየተሠራ መሆኑን ኢንጂነር ታመነ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡

ዕቅዱን ለማሳካትም በክልሉ በየደረጃው ያሉ የሥራ ኃላፊዎች፣ ባለ ድርሻ አካላትና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች በገንዘብ፣ በእውቀት እና በጉልበት አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ቢሮው ጥሪ አቅርቧል፡፡

በዮሐንስ ደርበው

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.