Fana: At a Speed of Life!

የዓድዋ ድል ላይ ያተኮረ ሀገር አቀፍ የፓናል ውይይት መካሄድ ጀመረ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 22፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የመከላከያ ሚኒስቴር ያዘጋጀው 127ኛው የዓድዋ ድል ላይ ያተኮረ ሀገር አቀፍ የፓናል ውይይት በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ መምሪያ እየተካሄደ ነው።

የዓድዋ ድል 127ኛ ዓመት “ዓድዋ አንድነት፣ ጀግንነት እና ጽናት” በሚል መሪ ሀሳብ በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ነው።

በውይይቱ ላይ የመከላከያ ሚኒስትር አብርሃም በላይ፣ የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴን ጨምሮ ጄነራል መኮንኖችና የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም የታሪክ ምሁራን ተገኝተዋል።

በውይይቱ ላይ የመከላከያ ጥናትና ምርምር ማዕከል ኃላፊ ብርጋዴር ጄነራል ይታያል ገላው፣ የአድዋ ድል ከኢትዮጵያ አልፎ የአፍሪካውያን የነፃነት ቀንዲል ነው ብለዋል።

ድሉን ተከትሎ አፍሪካውያን የፀረ-ቅኝ ግዛት ተጋድሎ ለማድረግ ወታደራዊ የሥልጠና መነሻ እንደሆነም ጠቅሰዋል።

ድሉ ለዚህ ዘመን ኢትዮጵያውያንም የአሸናፊነት ስነ-ልቦና ማስታጠቁን ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያውያን ከአራቱም ማዕዘን ወደ አድዋ በመትመም ጠላትን አሸንፈው ሀገራቸውን ማስከበራቸው ተገልጿል፡፡

እኛ የዚህ ዘመን ሠራዊትና ሌሎች ኢትዮጵያውንም የበለፀገችና ጠንካራዋን ኢትዮጵያ መመስረት ይኖርብናል ብለዋል ብርጋዴር ጄነራል ይታያል።

በውይይቱ ላይ የአድዋ ጦርነትና የሠራዊቱ ታሪክ እንዲሁም አድዋ የነፃነታችን መሠረትና የጥቁር ሕዝብ ኩራት በሚሉ ርዕሰ-ጉዳዮች ላይ ጥናታዊ ጹሑፎች እንደሚቀርቡ ኢዜአ ዘግቧል፡፡

 

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.