Fana: At a Speed of Life!

የአሁኑ ትውልድ ከዓድዋ ድል ትምህርት በመውሰድ ለሀገር ግንባታ በጋራ መነሳት አለበት – አቶ ኡሞድ ኡጁሉ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 22፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአሁኑ ትውልድ ከዓድዋ ድል ትምህርት በመውሰድ እና በፍቅር በመተሳሰር ለሀገር ግንባታ በጋራ መነሳት እንዳለበት የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ገለፁ።

ርዕሰ መስተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ ለ127 ኛው የዓድዋ ድል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመልዕክታቸውም የዓድዋ ድል ከኢትዮጵያ አልፎ በመላው ዓለም የሚገኙ ጥቁር ህዝቦች “እኔ ጥቁር ነኝ ግን ጠንካራ እና ውብ ነኝ” እንዲሉ ያስቻለ ነው ብለዋል።

“በዓድዋ ድል ጀግኖች አባቶች እና እናቶች ደማቸውን አፍስሰው አንገታችንን ቀና እንድናደርግ ስላስቻሉን ክብርና ምስጋና ይገባቸዋል” ሲሉም አውስተዋል።

የአሁኑ ትውልድ ከዓድዋ ድል ትምህርት በመውሰድ እና በፍቅር በመተሳሰር ለሀገር ግንባታ በጋራ መነሳት እንዳለበትም አስገንዝበዋል፡፡

በዓድዋ ጦርነት የውጭ ወራሪ የነበረው የጣሊያን ጦር ድባቅ ተመቶና ሽንፈትን ተከናንቦ የተመለሰበት መሆኑን ጠቁመው፥ ድሉ ለአፍሪካውያንም ትልቅ ድል መሆኑን አስታውሰዋል፡፡

“ድሉ በቆዳ ቀለም ላይ የተመሰረተውን የብቃት ደረጃ ልዩነት አስተሳሰብን የሻረ፣ የነፃነት ትግል እንዲነቃቃ ያደረገ እና የተረሳውን ታሪካችንን ሁል ጊዜ እንዲታወስ ያደረገ” መሆኑንም አብራርተዋል።

“ለዚህ ድል ያበቃንን በብዝሃነታችን ውስጥ ያለውን አድነታችንን በመጠበቅ የአድዋን ድል በድህነትና ኋላቀርነት ላይ ልንደግመው ይገባል” ብለዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.