Fana: At a Speed of Life!

የዓድዋ ድል የሰው ልጆችን የነፃነት ታሪክ የቀየረ ነው – ረዳት ፕ/ር አደም ካሚል

አዲስ አበባ፣ የካቲት 22፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓድዋ ድል በዓለም አቀፍ ደረጃ የእኩልነት፣የፍትህ እና የነፃነት ትግልን በማስፋፋት የሰው ልጆችን የነፃነት ታሪክ የቀየረ ነው ሲሉ የታሪክ ምሁሩ ረዳት ፕሮፌሰር አደም ካሚል ተናገሩ፡፡

የታሪክ ምሁሩ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደተናገሩት፥ የዓድዋ ጦርነት በቅኝ ግዛት ቀንበር ውስጥ ለነበሩ መላው አፍሪካውያን አዲስ የነፃነት ምዕራፍ የከፈተ ነው ብለዋል፡፡

የዓድዋ ድል በኋላ ቀር የአኗኗር ዘዴ ውስጥ ይኖር የነበረውን ማህበረሰብ ወደ አንድነት ያመጣ እና የአፍሪካውያንን አስተሳሰብ የቀየረ ስለመሆኑም አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በዓድዋ ጦርነት ድል ማድረጓ በቅኝ ያልተገዛች ብቸኛ አፍሪካዊት ሀገር እንድትሆን ማስቻሉን እና ድሉ ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃ የጥቁር ህዝቦች የነጻነት ምልክት እንድትሆን ማድረጉን አብራርተዋል፡፡

አፍሪካውያን ለነፃነት በሚያደርጉት ተጋድሎ ኢትዮጵያ እርዳታ ታደርግ እንደነበር ያስታወሱት የታሪክ ምሁሩ ኢትዮጵያ አፍሪካውያን ከቅኝ ግዛት እንዲላቀቁ ከፍተኛ ሚና መጫወቷን አንስተዋል፡፡

በዓድዋ ድል ምክንያት በርካታ የአፍሪካ ሀገራት የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ መሰረት በማድረግ የብሄራዊ ሰንደቅ አላማቸውን ቀለሞች መምረጣቸውን ጠቅሰዋል።

የዓድዋ ድል ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለነፃነት ፈላጊዎች በሙሉ ኩራት መሆኑን የገለፁት ምሁሩ የዓድዋ ድል ትልቅ ታሪካዊ ሀብት እና የሰው ልጆች የታሪክ ሂደትን በመቀየር ረገድ ትልቁ ምዕራፍ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

በዮናታን ዮሴፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.