የሀገር ውስጥ ዜና

127ኛው የዓድዋ ድል በዓል በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች በድምቀት እየተከበረ ነው

By Alemayehu Geremew

March 02, 2023

አዲስ አበባ፣ የካቲት 23፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) 127ኛው የዓድዋ ድል በዓል በአማራ ክልል ባህረዳር፣ ጎንደርና ደብረ-ብርሃን እንዲሁም በሌሎች የአማራ ክልል የተለያዩ ከተሞች በተለያዩ መርሐ-ግብሮች እየተከበረ ነው፡፡

የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ዶ/ር ድረስ ሳኅሉ በበኩላቸው ÷ ዓድዋ ለሰው ልጆች እኩልነትን ያረጋገጠ ትልቅ ድል ነው ብለዋል፡፡

ዓድዋ የአፍሪካውያንን ሥነ-ልቦና የመለሰና ያበረታ ፣ለኢትዮጵያውያን አንድነትን ያስተማረ ፣ለመሪዎች የመሪነት ጥበብን ያሳየ ድንቅ የአልበገርም ባይነት የድል በዓል መሆኑን ጨምረው ተናግረዋል።

በበዓሉ መርሐ-ግብር ላይ የባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ መምህር ዶ/ር የሻምበል አጉማሴ “አድዋ አንድነት ፣ጀግንነትና ጽናት” በሚል ርዕስ ፅሁፍ አቅርበው የሞቀ ውይይት ተካሂዶ እንደነበርም የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመለክታል።

የጎንደር ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ባዩህ አቡሃይ በበኩላቸው ÷ የዓድዋ ድል ታላቅ የጥቁር ህዝቦች ድል እንደሆነ አመላክተዋል፡፡

አክለውም ፥ ድሉ በመላው ዓለም ፖለቲካ ላይ ፣ በታሪክ መዛግብት እንዲሁም በሚታተሙ ሥነ-ፅሁፎች ከፍተኛ የዕይታ ለውጥ ያስከተለ ነው ብለዋል፡፡

የዓድዋ ድልን በየዓመቱ በድምቀት በማክበር አዲሱ ትውልድ የማንነቱን ታላቅነት ከቀደምት አባቶቻችን እያዋረስን የራሳችን ዘርፈ ብዙ ‘’አድዋዊ’’ ድል ማስመዝገብ ይገባልም ብለዋል፡፡

የቀደምት አባቶቻችንን ሀገር የማፅናት ተጋድሎ የምናስቀጥል የቁርጥ ቀን ልጆች መሆናችንን በምግባራችን አፅንተን ለኢትዮጵያ አሻራችንን ልናሳርፍ ይገባልም ማለታቸውን ከከተማው ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በበዓሉ ንግግር ያደረጉት የደብረብርሃን ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ካሳሁን እምቢያለ ÷ 127ኛው የዓድዋ ድል በዓል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ክብር ማኅተም እንዲሁም የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ተጋድሎ ቀንዲል ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

አቶ ካሳሁን ፥ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የሃሳብ ልዩነት ቢኖራቸውም ለሀገራቸውና ለህዝባቸው ነፃነት ግን በጋራ እንደሚቆሙም አንስተዋል፡፡

127ኛው የዓድዋ ድል በዓል በወረ-ኢሉም በደማቅ ሁኔታ እየተከበረ ሲሆን ከተማዋ የዓድዋ ጦርነት ዘማቾች መሰባሰቢያ ቦታ ሆና ማገልገሏንም ገልጸዋል፡፡

አድዋ የአንድነት እንጂ የመለያየት መልክ የለዉምና ሁሉም ኢትዮጵያዊ አንድነቱን ማረጋገጥ አለበት ሲሉም የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱ ሁሴን ተናግረዋል፡፡

የአማራ ክልል መንግስት ኮሚኒኬሽን ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ኅሊና መብራቱ በበኩላቸዉ ÷ ዓድዋ ኢትዮጵያን በዓለም ያገነነ የድል በዓል ነዉ ፤ አሁንም ትዉልዱ በዞኑ ያሉ የዓድዋ መታሰቢያዎችን መንከባከብ ይገባዋል ብለዋል፡፡