የሲሚንቶ እጥረት እንዳይከሰት አምራች ፋብሪካዎችን በመደገፍ እየተሰራ መሆኑን የማዕድን ሚኒስቴር ገለጸ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 23፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሀገሪቱ የሲሚንቶ እጥረት እንዳይከሰት አምራች ፋብሪካዎችን በመደገፍ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የማዕድን ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከሲሚንቶ አምራቾች ማህበር ጋር የሲሚንቶ ግብይትን ለመቆጣጠር ባወጣው መመሪያ ቁጥር 940/2015 መሰረት የሲሚንቶ የግብይትና ስርጭት አሰራር ስርዓትን በመዘርጋት ክትትል እንደሚደረግ አስቀምጧል።
ይሁን እንጂ በአዲስ አበባ ሲሚንቶ የለም በሚል ምክንያት በአንድ ኩንታል ከ1 ሺህ 730 እስከ 1 ሺህ 850 ብር ዋጋ ጨምሮ በጥቁር ገበያ የመሸጥ ሒደት መኖሩን ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ቅኝት ባደረገባቸው የሲሚንቶ የችርቻሮ መሸጫዎች ቦታዎች ተመልክቷል።
በመገናኛ፣ ሃይሌ ጋርመንት ፣ ጎሮ እና ተክለሃይማኖት አካባቢ ከተቀመጠው ተመን በላይ ሲሚንቶ የሚሸጡ አካላት ላይ ጥብቅ ቁጥጥር በማድርግ እርምጃ ከመውሰድ አንጻር ክፍተቶች መኖራቸውንም ለመታዘብ ተችሏል፡፡
የሲምንቶ አምራቾች ማህበር ምክትል ፕሬዚዳንት ገዛኸኝ ደቻሳ ÷ አከፋፋዮችና ቸርቻሪዎች በመመሪያው መሰረት በተቀመጠ የዋጋ ተመን ተከትለው ግብይት እንዲፈጽሙ መመሪያ መሰጠቱን ገልጸዋል።
የሲሚንቶ እጥረት እንዳይከሰት ፋብሪካዎቹ የሚያጋጥማቸውን የፀጥታና የማሽነሪ ብልሽት ችግር ተቋቁመው ምርት እያመረቱ እንደሚገኙም አብራርተዋል።
ቁጥጥሩን ከማጠናከር አንጻር ከተለያዩ ተቋማትና ጸጥታ አካላት ጋር የተቀናጀ የቁጥጥር ስራ መጀመሩን የተናገሩት ደግሞ የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ሃላፊ አቶ አደም ኑሪ ናቸው።
አቶ አደም ኑሪ ከተቀመጠው ተመን በላይ ሲሸጡ በሚገኙ ነጋዴዎች ላይ የማያዳግም እርምጃ እንደሚወሰድ አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ስራዎች ጅርጅትም የሲሚንቶ እጥረት እንዳይከሰት ገበያ ለማረጋጋት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የድርጅቱ የኦፕሬሽን ዘርፍ ም/ዋና ስራ አስፈጻሚ ቀፀላ ሸዋረጋ ÷ የሲሚንቶ ገበያን ለማረጋጋት ለፋብሪካዎቹ አስቀድሞ ክፍያ የተፈጸመ ቢሆንም ዳንጓቴና ሙገር ፋብሪካዎች ብቻ በሳምንት በአንድና ሁለት ተሽከርካሪ ሲሚንቶ እንደሚያስረከቡ ተናግረዋል።
በተቻለ አቅም በሚያገኙት ሲሚንቶ መጠን ለተፈቀደላቸው በግንባታ ዘርፍ ለሚገኙ አካላት እየሸጡ መሆኑን አስረድተዋል።
የማዕድን ሚኒስትር ዴኤታ ሚሊዮን ማቲዮስ በበኩላቸው፥ በሀገሪቱ የሲሚንቶ እጥረት እንዳይከሰት አምራች ፋብሪካዎችን በመደገፍ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በማሽነሪ ብልሽት ምክንያት የውጭ ምንዛሬ የሚያስፈልጋቸው ሲሚንቶ አምራቾችን ለመደገፍ ከብሔራዊ ባንክና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የፀጥታ ችግር ያለባቸው ፋብሪካዎች አካባቢ ችግሮችን ለመቅረፍ የፌደራል መንግስት ከክልል መንግስታት በጋራ በጥምረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
በአማራና በሌሎችም ቦታዎች ወደ ዘርፉ የሚገቡ አዳዲስ ፋብራካዎች በፍጥነት ወደ ምርት እንዲገቡ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑንም አረጋግጠዋል።
በቀጣይ ዘርፉ ላይ መዋዕለ ንዋያቸውን ለሚያፈሱ አካላት አስፈላጊው እገዛ እንደሚደረግም አንስተዋል፤፡፡
በታሪክ አዱኛ