Fana: At a Speed of Life!

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልና የብሉ ናይል ግዛት የሕዝቦችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ስራዎችን በጋራ ለመስራት ተስማሙ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 23፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እና የብሉ ናይል ግዛት የሕዝቦችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ስራዎችን በጋራ ለመስራት ስምምነት ተፈራረሙ።

የሁለቱ ክልሎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በደማዚን ከተማ ለሁለት ቀናት ሲያካሂዱት የነበረው የምክክር መድረክ ዛሬ ተጠናቋል።

ባለፉት ጊዜያት በጋራ ታቅደው የተከናወኑ ስራዎችን የገመገሙት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎቹ፣ በቀጣይ የሁለቱን ተጠቃሚ ለማድረግ በጋራ የሚከናወኑ የጸጥታ፣ የኢኮኖሚ እና የማኅበራዊ ስራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል ስምምነት ተፈራርመዋል።

ስምምነቱን በኢትዮጵያ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን እና በሱዳን የብሉናይል ግዛት ፕሬዚዳንት ጀነራል መሐመድ አልዑምዳ ተፈራርመዋል።

ስምምነቱ የድንበር አካበባቢዎችን ጨምሮ በሁለቱ ክልሎች ሠላምን በማረጋገጥ ሕዝቦቹን በኢኮኖሚ እና በማኅበራዊ ዘርፎች የበለጠ ለማስተሣሠር እና ተጠቃሚ ለማድረግ ያለመ ነው ተብሏል።

የሁለቱ ክልሎች መንግስታት ስምምነቱ ተግባራዊ ለማድረግ በቁርጠኝነት እንደሚሠሩ አረጋግጠው÷የዕቅዱን ተግባራዊነት በየስድት ወሩ እየተገናኙ እንደሚገመግሙም አስታውቀዋል።

የብሉናይል ግዛት ፕሬዚዳንት ጀነራል መሐመድ አልዑምዳ ለቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን የክብር ሽልማት እና የምስጋና መርሐ-ግብር አካሂደዋል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን፣ ከአቀባበሉ ጀምሮ ለተደረገላቸው እጅግ የላቀ አክብሮት በክልሉ መንግስት ስም ምስጋና ማቅረባቸውንም የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.