ቻይና እና ህንድ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ተስማሙ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 24፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ቻይና እና ህንድ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር መስማማታቸውን የሁለቱ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች አስታውቀዋል፡፡
የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቂን ጋንግ እና የህንድ አቻቸው ሱራህማንያም ጃይሻንካር በህንድ ኒው ደልሂ ከተካሄደው የቡድን 20 አባል ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ ጎን ለጎን ውይይት አድርገዋል፡፡
በውይይታቸው የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቂን ጋንግ በፍጥነት እያደገ ያለ ኢኮኖሚ ያላቸው ሁለቱ ሀያላን ሀገራት ብዙ የጋራ ፍላጎቶች አሏቸው ብለዋል፡፡
የሁለቱ ሀገራት የእድገት መነቃቃት የዓለምን አንድ ሶስተኛ ህዝብ እንዲሁም የእስያ አህጉር እና የዓለምን የወደፊት እጣ ፋንታ የሚወስን መሆኑን አመላክተዋል፡፡
የሁለቱ ሀገራት መሪዎች ያደረጓቸው ስምምነቶች ወደ ተግባር እንዲገቡ፣ውይይቶች እንዲቀጥሉ እና የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት እንዲጠናከርም አስገንዝበዋል።
የህንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሱራህማንያም ጃይሻንካር በበኩላቸው ህንድ እና ቻይና ታላቅ የጥንታዊ ስልጣኔ ባለቤቶች መሆናቸውን አንስተዋል።
ሁለቱም ወገኖች በኢኮኖሚያዊ ትብብር ፣በህዝብ ለህዝብ እና በባህል ልውውጦች አወንታዊ ውጤቶችን ለማምጣት እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡
በውይይቱ ከቻይናው አቻቸው ጋር የሁለቱ ሀገራት የሁለትዮሽ ግንኙነት ከታሪክና ከስትራቴጂያዊ አጋርነት እይታ አንፃር እንዲታይ እና እንዲሻሻል እንዲሁም የህንድና ቻይና የትብብር መድረኮች እንዲገነቡ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ገልፀዋል፡፡
በቻይና እና በህንድ መካከል ያለው የድንበር ግጭት እየተረጋጋ መምጣቱን የጠቆሙት ሚኒስትሩ ሁለቱም ወገኖች በድንበር አካባቢ ሰላምና ፀጥታን ለማስጠበቅ በጋራ ሊሰሩ ይገባል ማለታቸውን ሲ ጂ ቲ ኤን ዘግቧል፡፡