Fana: At a Speed of Life!

በ2035 ከግማሽ በላዩ የዓለም ህዝብ ከመጠን በላይ በሆነ ውፍረት ሊጠቃ እንደሚችል ሪፖርት አመላከተ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 24፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አስፈላጊው እርምጃ ካልተወሰደ በፈረንጆች 2035 ከግማሽ በላይ የሚሆነው የዓለም ህዝብ ከልክ በላይ በሆነ ውፍረት ሊጠቃ እንደሚችል የዓለም አቀፉ ከልክ በላይ ውፍረት ፌዴሬሽን ሪፖርት አመላከተ፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ የመጣው ከልክ በላይ ውፍረት በ2035 ከግማሽ በላይ የሆነውን የዓለም ህዝብ በተለይ ደግሞ ህጸናትን ሊያጠቃ እንደሚችል ፌዴሬሽኑ አስጠንቅቋል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ ከአራት ቢሊየን የሚበልጡ ሰዎች ከዚሁ ጋር በተያያዘ ችግር ሊዳረጉ እንደሚችሉም ነው ፌዴሬሽኑ በሪፖርቱ ያመላከተው።

ዝቅተኛ ወይም በጣም ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የአፍሪካ እና እስያ ሀገራት ላይ ደግሞ ጫናው ሊበረታ እንደሚችል ነው ሪፖርቱ የገለጸው፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ በሚከሰት ችግር ምክንያት በፈረንጆቹ 2035 ይህንን ችግር ለመቅረፍ የሚወጣው ወጪ በአመት ከ4 ትሪሊየን ዶላር በላይ እንደሚሆንም ነው የተነበየው፡፡

የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ሉዊዝ ባውር እንደገለጹት ሪፖርቱ ሃገራት ከመጠን ባለፈ ውፍረት ከሚመጣው አደጋ ከመጋለጣቸው በፊት አስቀድመው እርምጃ እንዲወስዱ ለማስጠንቀቅ ያለመ ነው ፡፡

በተለይ ሪፖርቱ በህጻናት እና ታዳጊዎች ላይ ከልክ ያለፈ ውፍረት እየጨመረ መምጣቱን ጠቅሰው፥ ቁጥሩ ከፈረንጆቹ 2020 አንጻር በህጻናት ወንዶችም ሆነ ሴቶች በእጥፍ እንደሚጨምርም ነው ነው የሚናገሩት።

በዓለም ዙሪያ ከመጠን በላይ ውፍረት መጨመር በኢኮኖሚው ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር የሪፖርቱ ግኝት ማመላከቱን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

ይህም ከዓለም ጠቅላላ የምርት እድገት 3 በመቶውን የሚሸፍን መሆኑን ነው ሪፖርቱ ያመላከተው።

የዚህ ችግር ሰለባ ከሆኑና በጣም ዝቅተኛ ወይም ዝቅተኛ ኢኮኖሚ ካላቸው ሀገራት መካከል ከ10 ዘጠኙ በአፍሪካ እና እስያ ይገኛሉ ነው የተባለው።

የተቀነባበሩ ምግቦችን አብዝቶ መመገብ፣ ረጅም ሰአት መቀመጥና የአካል ብቃት እንስቃሴ አለማድረግ፣ የምግብ ሸቀጥ ግብይቱን የሚቆጣጠር ጠንካራ ፖሊሲ አለመኖር እንዲሁም ክብደትን ለመቆጣጠርና የጤና ትምህርትን ማስረጽ የሚያስችል ጠንካራና የተደራጀ የጤና ስርአት አገልግሎት አለመኖር ደግሞ ለዚህ ችግር መንስኤ መሆኑ በሪፖርቱ ተመላክቷል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.