Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ በጋራ ለመሥራት ሥምምነት ተፈራረሙ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 24፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዲጂታል አሰራሮችን ለማስፋትና ለማጠናከር የሚያስችለውን የመግባቢያ ሥምምነት ከሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ጋር መፈራረሙ ተገለጸ።

ሥምምነቱን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቤ ሳኖና እና የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስኪያጅ አንዋር ሶሳ መፈረማቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የባንኩ ፕሬዚዳት አቶ አቤ ሳኖ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ÷ ባንኩ የደንበኞችን ፍላጎት ለማርካት የተለያዩ ዘመናዊ አሰራሮችን ተግባራዊ እያደረገ ነው።

የባንኩ ተቀማጭ ገንዘብ ከአንድ ትሪሊየን መሻገሩን ገልጸው ለዚህም የዲጂታል አገልግሎት መስጠት መጀመሩ ለስኬቱ የጎላ አስተዋጽዖ አበርክቷል ብለዋል።

አሁንም የተለያዩ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ተግባራዊ በማድረግ የአገልግሎት አሰጣጡን ይበልጥ ለማዘመን በትኩረት እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በመሆኑም ዛሬ የተደረሰው ሥምምነት በባንኩ የሚሰጣቸው አገልግሎቶች በዘመናዊ አሰራር የተደገፉ ለማድረግ እንደሚያግዝ ነው የተናገሩት።

የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስኪያጅ አንዋር ሶሳ በበኩላቸው ÷ በኢትዮጵያ የዲጂታል ተደራሽነት እየተስፋፋ መምጣቱ የሚበረታታ መሆኑን አንስተዋል።

በተለይም ”ዓለማችን በልዩ ልዩ የቴክኖሎጂ ሥራዎች አንድ እየሆነች በመጣችበት በዚህ ጊዜ አማራጮችን በማስፋት ተደራሽ ማድረግ የግድ ያስፈልጋል” ነው ያሉት።

ሳፋሪኮም ኢትዮጰያ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ያደረገው ሥምምነት ለዲጂታላይዜሽን ትግበራ ትልቅ አስተዋጽዖ እንዳለውም ነው የገለጹት።

ተቋማቸው ባንኩ በዲጂታል አሰራር መስጠት የሚፈልጋቸውን የትኛውንም አገልግሎቶች ተደራሽ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑንም ዋና ሥራ አስኪያጁ አረጋግጠዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.