የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ ቀዳሚው ተደራሽ አየር መንገድ መሆኑ ተነገረ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 24፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ በርካታ የአፍሪካ ሀገራትን በበረራ በመሸፈን ቀዳሚ መሆኑ ተገለጸ፡፡
በአፍሪካ አህጉር ከ25 በላይ መዳረሻዎችን የሚሸፍኑ አምስት አየር መንገዶች እንዳሉ ሲምፕል ፍላይንግ በመረጃው አመላክቷል፡፡
የአፍሪካ ዓየር መንገዶች ማኅበር ዋና ጸሐፊ አብዱራህማን በርቴ ፥ እንደ አፍሪካ አኅጉር በርካታ ሀገራትን የያዘ እና በበረራ የሚሸፍን ሌላ አኅጉር እንደሌለ በሞሮኮ በተካሄደው የበረራ መስመሮችን ማሳደግ ላይ የሚመክር ፎረም ላይ ጠቁመዋል፡፡
አፍሪካ በመጠን ደረጃ አሜሪካ፣ አውሮፓ እና ቻይና ተደምረው ካላቸው ጠቅላላ ስፋት ትልቃለች።
54 ሀገራትን ባቀፈውና በርካታ መዳረሻዎች ባሉት የአፍሪካ አቪየሽን ዘርፍም የኢትዮጵያ አየር መንገድ በበርካታ ሀገራት በረራ በማድረግ ቀዳሚው መሆኑን ያስረዳሉ።
የአፍሪካ አየር መንገዶች በአህጉር ደረጃ በሚያደርጉት በረራ አምስት ሀገራት ብቻ 25 እና ከዛ በላይ መዳረሻዎች አሏቸው ተብሏል።
በዚህም የኢትዮጵያ አየር መንገድ 38 አህጉራዊ መዳረሻዎች ሲኖሩት ይህም በአፍሪካ ቀዳሚው ያደርገዋል ነው የተባለው።
ኬንያ ኤር ዌይስ 28፣ የደቡብ አፍሪካ አየር መንገድ 27፣ የሞሮኮው ሮያል ኤር ሞሮኮ 26 እንዲሁም የቶጎው አስኪ 25 በረራዎችን በማድረግ ተከታዮቹን ደረጃዎች ይዘዋል።