የፌዴራልና ክልል ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ተቋማት የ6 ወራት የዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ ፣ የካቲት 25 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት የተዘጋጀው የፌዴራልና ክልል ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ተቋማት የበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ 6 ወራት የዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ እየተካሄደ ነው።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ እንዳሉት፥ ኢትዮጵያ በጫናዎች ውስጥ ሆናም በተለያዩ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ተጨባጭ ለውጥ ተመዝግቧል።
በኢትዮጵያ ባለፉት ስድስት ወራት በሀገራዊ ዕድገትና ገጽታ ግንባታ ላይ ጠንካራ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ስራ መከናወኑንም ነው የገለጹት።
በኢትዮጵያ በስንዴ ልማት፣ በመልካም አስተዳደር ስራዎች፣ በአገልግሎት አሰጣጥና በዲፕሎማሲያዊ ጉዳዮች አበረታች ውጤት ተገኝቷል ብለዋል።
ሰላምና መረጋጋትን በማስፈን በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር እንደ ሀገር የተመዘገቡ ስኬቶች መሆናቸውንም ጠቁመዋል።
በመንግሥትና ህወሐት መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት መሰረት እንዲይዝ እንዲሁም በሌሎች ሀገራዊ ስኬቶች ላይ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ ጠንካራ ስራ ማከናወኑንም ጠቅሰዋል።
በኢትዮጵያ አክራሪነትና ጽንፈኝነት ውስብስብ ችግሮችን በመፍጠር ተፅዕኖ ማሳደራቸውን የገለፁት ሚኒስትሩ ይህን በመመከትም አበረታች ስራ ተሰርቷል ነው ያሉት።
በቀጣይም አክራሪነትና ፅንፈኝነትን በቅንጅት በመመከት የኢትዮጵያን ህዝብ የሚመጥን የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ስራ መስራት እንደሚገባ ማሳሰባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።