Fana: At a Speed of Life!

የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት መሻሻል ቢያሳይም ካለው ፍላጎት ጋር አይመጣጠንም – የትግራይ ክልል ነዋሪዎች

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 25 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ የሰብዓዊ ድጋፎች አቅርቦት መሻሻል ቢያሳይም ካለው ፍላጎት ጋር እንደማይመጣጠን የትግራይ ክልል ነዋሪዎች ተናገሩ።

በሰሜን የነበረውን ግጭት ተከትሎ ከአምራችነት ወደ ተረጂነት መቀየራቸውን የተናገሩት ነዋሪዎቹ ወደ መደበኛ ስራዎቻቸው የመመለስ ፍላጎታቸውን አስረድተዋል።

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በክልሉ ባደረገው ቅኝት የረድኤት ስራዎች በመንግስትና አጋር ድርጅቶች እየተከወኑ መሆናቸውን ተመልክቷል።

ሆኖም ነዋሪዎቹ እየተደረገ ያለው ድጋፍ መሻሻሎች ቢያሳይም ጊዜውን ጠብቆ ከመቅረብና ከመጠን አንፃር በቂ እንዳልሆነ ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ከእርዳታው ጋር ተያይዞ በእርዳታ ማዕቀፍ ያልተካተቱ ሰዎች መኖራቸውንም ነው የተናገሩት።

በሽሬ ከተማ የሰብዓዊ ድጋፍ አስተባባሪ ታዬ ማሞ በድጋፍ አሰጣጡ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች መኖራቸውን አረጋግጠዋል።

ችግሩ የተፈጠረው የተረጂዎች ቁጥር መረጃ ሲያዝ አብዛኛዎቹ ነዋሪዎች ከአካባቢው ተፈናቅለው በመቆየታቸው፣ መንግስታዊ መዋቅሮች በመፍረሳቸውና የተረጂዎች ቁጥርና አቅርቦቱ ባለመጣጠኑ ነው ብለዋል።

አሁን ላይ የተረጂዎች ቁጥር ማሻቀቡን በመጥቀስም፥ ላለፉት ስድስት ወራት ከጊዜያዊ ነፍስ አድን ድጋፍ የዘለለ መደበኛ ድጋፍ አለመደረጉን አስረድተዋል።

ዓለም አቀፍ ደረጃውን ያሟላ ድጋፍም ከትናንት ጀምሮ በሽረና አካባቢው ለ140 ሺህ ዜጎች መደረግ መጀመሩን ነው የተናገሩት።

ነዋሪዎቹ በእርዳታ ዘላለም መኖር ስለማይቻል ወደ መደበኛ ህይወታቸው ለመመለስ የተጀመረው ሰላም እንዲጠናከርም ጠይቀዋል።

በአፈወርቅ እያዩ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.