በሃረሪ ክልል በደረሰ የትራፊክ አደጋ የዘጠኝ ሰዎች ህይወት አለፈ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 25፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሐረሪ ክልል በደረሰ የትራፊክ አደጋ የዘጠኝ ሰዎች ህይወት ማለፉን የክልሉ ፖሊስ አስታወቀ።
አደጋው የደረሰው በክልሉ ሶፊ ወረዳ በተለምዶ ሃረዌ ሳልቶ በተባለው ስፍራ ትላንት ሌሊት 9 ሰዓት አካባቢ መሆኑን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የትራፊክ አደጋ መርማሪ ዋና ሳጅን ረስተም መዝሃር ገልጸዋል።
ከድሬዳዋ ወደ ጅግጅጋ ከተማ ሲጓዝ የነበረ የጭነት ተሽከርካሪ ፍሬን ሾፌሩ መቆጣጠር ባለመቻሉ መንገድ ስቶ በመውጣት ባስከተለው ግጭትም አደጋው መድረሱን አስረድተዋል።
በዚህም ሾፌሩና ከመንገድ ውጭ ተኝተው የነበሩ ስምንት ግለሰቦች ህይወታቸው ማለፉን አስታውቀዋል።
በአደጋው ከባድና ቀላል ጉዳት የደረሰባቸው ሁለት ግለሰቦች የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል፡፡