ያልተጠናቀቁ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግምባታ እስከ ሰኔ ወር እንዲጠናቀቅ ከንቲባ አዳነች አሳሰቡ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 26፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ያልተጠናቀቁ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግምባታ እስከ ሰኔ ወር እንዲጠናቀቅ አሳሰቡ፡፡
የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ግንባታ በተያዘላቸው ጊዜ ያለማጠናቀቅ ክፍተት እንዳለ መገምገሙን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናግረዋል፡፡
ለዚህ ክፍተትም የሲሚንቶ እጥረት፣ የተለያዩ የግምባታ ግብዓቶች ዋጋ ልዩነት እንዲሁም የወሰን ማስከበር ችግር መኖሩን ተገንዝበናል ነው ያሉት፡፡
ሆኖም እነዚህን ችግሮች በመቅረፍ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን መሰረታዊ ግንባታ መንግስት በአፋጣኝ በማጠናቀቅ ቀሪውን ተጠቃሚው እንዲያሟላ የሚደረግ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የመሰረተ ልማት አቅራቢ ተቋማት ቀሪ ስራዎችን በቅንጅትና በፍጥነት እንዲያጠናቅቁ አቅጣጫ የተቀመጠ ሲሆን÷ ይህንንም የሚከታተሉ ተቋማትና ኮሚቴዎች በየሳምንቱ የግንባታውን ሂደት ይከታተላሉ ተብሏል።
የተነሱት የግብዓት እጥረትና የዋጋ ልዩነቶችም አፋጣኝ እልባት አግኝተው እስከ ሰኔ ወር ባለው ግዜ ግንባታዎች ተጠናቅቀው ለተጠቃሚው ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጡ አቅጣጫ መቀመጡንም የከንቲባ ጽ/ቤት መረጃ ያመላክታል።