ሀገር አቀፍ የባሕል ስፖርቶች ውድድርና ፌስቲቫል በሚዛን አማን ተጀመረ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 26፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) 20ኛው ሀገር አቀፍ የባሕል ውድድርና 16ኛው የባሕል ፌስቲቫል “ባሕላዊ ስፖርቶች ለአንድነታችንና ለሠላማችን” በሚል መሪ ቃል በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሚዛን አማን ከተማ ተጀመረ፡፡
የባሕልና ስፖርት ሚኒስትር ቀጄላ መርዳሣ በመርሐ ግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር÷የባሕል ስፖርቶች ውድድርና የባሕል ፌስቲቫሎች ለሀገር ገጽታ ግንባታ የላቀ አስተዋጽኦ አላቸው ብለዋል፡፡
ውድድሩ ለሀገር ገጽታ ግንባታ ከሚያበረክተው አስተዋፅዖ ባለፈ አብሮነትን በማጠናከር የብሔር ብሔረሰቦች ባሕልን ለትውልድ ለማስተዋወቅ እንደሚያግዝም ነው የገለጹት፡፡
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ፥ የሰው ልጆችን አኩሪ ባሕል ለመጠበቅ፣ ወደ ቀጣዩ ትውልድ እንዲሸጋገር ለማስቻል እና በክልሉ የሚኖሩትን ብዝኃ ብሔረሰቦች አንድነት ለማጠናከር በቀጣይ በተቀናጀ መንገድ ይሰራል ብለዋል፡፡
20ኛው ሀገር አቀፍ የባሕል ውድድርና 16ኛው የባሕል ፌስቲቫል እስከ መጋቢት 3 ቀን 2015 ዓ.ም እንደሚቆይ ደሬቴድ ዘግቧል።