Fana: At a Speed of Life!

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ከሠመራ ዩኒቨርሲቲ ጋር በትብብር ለመስራት ተፈራረመ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 27፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ከሠመራ ዩኒቨርሲቲ ጋር በጋራ ለመስራት የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርሟል።

ስምምነቱን የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አድማሱ ዳምጠው እና የሠመራ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት አብዱራህማን ከድር ተፈራርመዋል።

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት አስተማሪ፣ ወቅታዊ ፣ አዝናኝ እና መሰል ጉዳዮችን በተለያዩ ቋንቋዎች ለማህበረሰቡ ተደራሽ የማድረግ የካበተ ልምድ እንዳለው ያነሱት አቶ አድማሱ ተደራሽ ከሚያደርጋቸው ቋንቋዎች መካከል በአፋርኛ ቋንቋ ከ20 አመት በላይ ልምድ እንዳለው አውስተዋል።

ስምምነቱ በዩኒቨርሲቲው የሚሰሩ የማህረሰብ አቀፍ እና የምርምር ስራዎችን እና የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ስራዎችን ለማህበረሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ያለመ ነው ብለዋል፡፡

ከዩኒቨርሲቲው ጋር በጋራ በመሆን የዩኒቨርሲቲውና የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ የሚያደርግ የማህበረሰብ ሬድዮ ለመጀመር እና በክልሉ የሚሰሩ የልማት ስራዎችን ለማህበረሰቡ ተደራሽ ለማድረግ እንደሚያግዝም ነው የተናገሩት።

የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት አብዱራህማን ከድር በበኩላቸው÷ ዩኒቨርሲቲው ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በጋራ መስራቱ ከመማር ማስተማር ስራው ጎን ለጎን እየሰራቸው ያሉ ስራዎችን ለማህበረሰቡ ለማድረስ የማይተካ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።

በዩኒቨርሲቲው ውስጥ የማህበረሰብ ሬዲዮ ለማቋቋም ለሚደረገው ጉዞም ስምምነቱ ፋይዳ እንደሚኖረው አንስተዋል።

በሳሙኤል ወርቃየሁ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.