ከ522 ሺህ በላይ ዶላር አሽሽተዋል የተባሉ ነጋዴዎችና የጉምሩክ ሰራተኞች የሙስና ወንጀል ክስ ቀረበባቸው
አዲስ አበባ፣ የካቲት 27፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ522 ሺህ በላይ የአሜሪካ ዶላር በማሸሽ ሀገሪቷን የውጭ ምንዛሬ አሳጥተዋል የተባሉ ነጋዴዎችና የጉምሩክ ሰራተኞች የሙስና ወንጀል ክስ ቀረበባቸው።
ክሱ የቀረበባቸው በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው።
ተከሳሾቹ ስድስት ሲሆኑ÷ ከዚህ በፊት በሌሎች ሁለት መዝገቦች በተመሳሳይ ተግባር በሙስና ወንጀል የተከሰሱት የጉምሩክ ኮሚሽን አዲስ አበባ ቦሌ ቅርንጫፍ ሰራተኞች ወተቱ አበበ እና አዲስ አለም ደረሰ ይገኙበታል።
ሌሎቹ ተከሳሾች ነጋዴዎች ሲሆኑ÷ አቶ ሙክታር መሀመድ ያሲን፣ መሰረት ንጉሴ፣ ወይዘሮ ሲትራ መሀመድ እና በተመሳሳይ የሙስና ወንጀል ተከሶ ማረሚያ ቤት የሚገኘው ዮናስ አምሳሉ ናቸው።
ተከሳሾቹ የተሳትፎ ደረጃቸው ተጠቅሶ በህገወጥ መንገድ የተገኘ ገንዘብን ወይም ንብረትን ህጋዊ አድርጎ በማቅረብ እና ሀሰተኛ ሰነድ መገልገል ተደራራቢ የሙስና ወንጀል ክስ ዛሬ ተመስርቶባቸዋል።
1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች በጉምሩክ ኮሚሽን አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሲሰሩ ከአስመጪ ነጋዴዎች ጋር በጥቅም በመመሳጠር በተለያየ ጊዜ ነጋዴዎቹ የጉዞ ታሪክ ሳይኖራቸው እንዳላቸው በማስፈር እና ከውጭ ሀገር ያላስገቡትን ዶላር እንዳስገቡ አስመስለው ዲክሌር አድርገዋል ተብለው ተደራራቢ የሙስና ወንጀል ክስ ቀርቦባቸዋል።
ከ3ኛ አስከ 6ኛ የተጠቀሱ ነጋዴዎች ደግሞ በተለያየ መጠን ከጥቁር ገበያ የሰበሰቡትን ከ522 ሺህ 100 የአሜሪካ ዶላር በላይ ከውጭ ሀገር እንዳስገቡ በማስመሰል እና ሀሰተኛ የጉምሩክ ዲክላራሲዮን ሰነድ በመጠቀም በጉምሩክ ሰራተኞች ዲክሌር በማስደረግ ገንዘቡን በማሸሽ ለግል ጥቅም በማዋል በመንግስትና በህዝብ ጥቅም ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሰዋል ተብለው ነው የተከሰሱት፡፡
ከስድስቱ ተከሳሾች መካከል በሌላ ተመሳሳይ ተግባር በሙስና ክስ ወንጀል የተከሰሱት 1ኛ፣ 2ኛ እና 6ኛ ተከሳሾች ዛሬ በችሎት አልቀረቡም፡፡
ቀሪ ተከሳሾች ግን ችሎት ቀርበው ክሱ እንዲደርሳቸው ተደርጓል።
ክሱ በችሎት በንባብ የተሰማ ሲሆን ፍርድ ቤቱ ዛሬ የቀረቡ ተከሳሾች የክስ መቃወሚያ ካላቸው ለመጠባበቅ ለመጋቢት 1 ቀን 2015 ዓ.ም ቀጥሯል።
ላልቀረቡ ተከሳሾችም መጥሪያ እንዲደርስ ታዟል።
በታሪክ አዱኛ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-