Fana: At a Speed of Life!

የነርቭ ህመም መንስኤ ምንድን ነው?

አዲስ አበባ፣ የካቲት 28፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ‘የነርቭ ህመም’ ተብሎ በተለምዶ እንደ አንድ ነጠላ ህመም ይጠራ እንጂ የነርቭ ሥርዓት አካል (የኒውሮሎጂካል) ህመሞች በርካታ ናቸው፡፡
በየትኛውም የነርቭ ሥርአት አካል (ነርቨስ ሲስተም) ላይም እንደሚከሰቱ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
የነርቭ ሥርአት አካል (ነርቨስ ሲስተም)÷ አንጎልን፣ ህብለሰረሰርን፣ ከአንጎልና ከህብለሰረሰር የሚወጡና የሚገቡ ነርቮችን፣ የነርቭና የጡንቻ መገናኛን፣ ጡንቻን እና ሌሎች ከዚህ ሥርአት ጋር ግንኙነት ያላቸውን አካላት ሁሉ ያጠቃልላል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የኒውሮሎጂ ሐኪም እና የኢትዮጵያ ኒውሮሎጂስቶች ማኅበር ፕሬዚዳንት ረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር ሐና ደምሴ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ÷ የነርቭ ሥርአት ህመሞች ዓይነታቸው እና መንስኤዎቻቸው የተለያየ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡
ህመሞቹ እደሚከሰቱበት ሁኔታ እና የጊዜ ቆይታም በተለያየ ምድብ ተከፍለው እንደሚታዩ ነው ባለሙያዋ የገለጹት፡፡
ለአብነትም በደም ዝውውር መስተጓጎል ለምሳሌ በጭንቅላት ውስጥ ደም መፍሰስ፣ በሚጥል ህመም፣ በዕጢዎች፣ በተለያዩ መመርቀዝ (ኢንፌክሽኖች)፣ በሰውነት ንጥረነገሮች መዛባት (ለምሳሌ እንደ ስኳር አይነት ህመሞች) እና በሌሎች ህመሞች ምክንያት የሚከሰቱ ሊሆኑ ይችላሉ ብለዋል፡፡
ምልክቶቹም እንደ ህመሙ ዓይነት፣ የጉዳት መጠን እና ህመሙ ጉዳት እንዳደረሰበት የነርቭ ሥርዓት አካል የተለያዩ መሆናቸውን ነው የሚገልጹት።
የእጅና እግር አለመታዘዝ፣ ፊት ወደ አንድ ጎን መዞር፣ የእይታ መጉደል፣ የንግግር መስተጎጎል፣ መርሳት እንዲሁም እራስን እስከመሳት የሚያደርስ ምልክት እንደሚያሳይ አብራርተዋል፡፡
የሥርአተ ነርቭ አካል ህመሞች እንደሚከሰቱበት ሁኔታ ጊዜ የሚሰጡ እና ፍጹም ጊዜ የማይሰጡ መኖራቸውን ህብረተሰቡ ማወቅ እንዳለበት አስገንዝበዋል።
ለምሳሌ በጭንቅላት ውስጥ ደም መፍሰስ ምክንያት የሚከሰት የሥርአተ ነርቭ አካል ህመም በፍጹም ጊዜ የማይሰጥ እና በተከሰተበት ቅጽበት የአካል ክፍልን ለማዘዝ የማይቻልበት ደረጃ እንደሚያደርስ ይናገራሉ፡፡
በአንጻሩ በመመርቀዝ ምክንያት የሚከሰቱ የሥርአተ ነርቭ አካል ህመሞች እንደጉዳቱ መጠን ቢወሰኑም የተወሰነ ጊዜ ሊሰጡ እንደሚችሉ ነው የሚገልጹት፡፡
በአጠቃላይ የሥርአተ ነርቭ አካል ህመም ከሰከንድ እስከ ዓመታት ባለው ጊዜ የከፋ ጉዳት ያስከትላል ነው የሚሉት፡፡
ህክምናው በአብዛኘው ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚሰጥ አመላክተው÷ በሀገር ውስጥ የማይሰጡ ውስብስብ የነርቭ ህመም አይነቶች መኖራቸውንም ጠቁመዋል፡፡
ህመሞቹ እንዳይወሳሰቡ ህብረተሰቡ የትኛውም ህመም እና አደጋ ሲያጋጥመው የጉዳት መጠኑ ሳያይል ሕክምና ማድረግ እንደሚጠበቅበት ይመክራሉ፡፡
በሌላ በኩል ጤናማ አመጋገብን በማዳበር፣ ቅባት የበዛባቸውን ምግቦች በማስወገድ፣ አትክልትና ፍራፍሬን በማዘውተር ፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን በማድረግ እና ለሌሎች ህመሞች መከላከያነት የሚመከሩ ዘዴዎችን በመተግበር የሥርአተ ነርቭ አካል ህመምን መከላከል እንደሚቻል አስገንዝበዋል፡፡
በዮሐንስ ደርበው
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.