ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው በቦንጋ ከተማ ያስገነቡትን የዳቦ ፋብሪካ መርቀው ከፈቱ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 28፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው በቦንጋ ከተማ ያስገነቡትን የዳቦ ፋብሪካ መርቀውለአገልግሎት ክፍት አድርገዋል፡፡
የዳቦ ፋብሪካው በ2 ነጥብ 4 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን በቀን 300 ሺህ ዳቦ የማምረት አቅም ያለው ነው ተብሏል።
የቀዳማዊት እመቤት ፅህፈት ቤት በሀገሪቱ ለማስገንባት ካቀደው 12 ዳቦ ፋብሪካዎች ውስጥ በቦንጋ ከተማ ስድስተኛውን ነው መርቀው ለአገልግሎት ክፍት ያደረጉት።
የዳቦ ፋብሪካው በሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ድጋፍ የተገነባ ሲሆን የዱቄት ፋብሪካ እና የእህል ማከማቻንም ያጠቃለለ ነው።
የፋብሪካው ግንባታ ዳቦን በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ የኑሮ ውድነቱን ለማቅለል አላማ አድርጓል።
በተጨማሪም ቀዳማዊ እመቤቷ በቦንጋ ከተማ ለሚገነባው የአውሮፕላን ማረፊያ ማረፊያ መሰረተ ድንጋይ ጥለዋል።
የአውሮፕላን ማረፊያው ከከተማው 11 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ሲሆን ግንባታውን ለማከናወን የሚያስችሉ የምንጣሮ እና ቦታውን የማዘጋጀት ስራዎች እየተሰሩ መሆኑ ተገልጿል።
በ44 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው ግንባታው የቦንጋ ከተማን እና አካባቢውን የኢንቨስትመንት እድል ለማስፋት እንዲሁም የአካባቢውን የመስህብ ስፍራዎች የጎብኚዎች መዳረሻ ለማድረግ ለሚሰራው ስራ አጋዥ ነው ተብላል።
በሜሮን ሙሉጌታ