Fana: At a Speed of Life!

የቻይና ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በኢነርጂ ልማት ዘርፍ መሰማራት እንደሚፈልጉ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 28፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሐብታሙ ኢተፋ ከቻይና ዓለም አቀፍ የኢነርጂ ቡድን ሊቀመንበር ሉ ዢያንግ ጋር በኢነርጂ ኢንቨስትመንት ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡

በውይይቱ  ወቅት ኢንጂነር ሐብታሙ ኢተፋ እንደገለጹት÷ባለፉት ዓመታት የቻይና ኩባንያዎች በመሰረተ ልማት ግንባታ ዘርፍ ከፍተኛ ተሳትፎ አድርገዋል፡፡

በኢትዮጵያ በኢነርጂ ዘርፍ በርካታ የኢንቨስትመንት ዕድሎች መኖራቸውንም ነው ያብራሩት፡፡

በተለይ በቀጠናው የሃይል ትስስር በመፍጠር ኢትዮጵያን የአረንጓዴ ኢነርጂ ማዕከል ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው÷ የታዳሽ ኢነርጂ ለቀጠናው ሀገራት በማቅረብ የኢነርጂ ትስስርን በመፍጠር የካርቦን ልቀትን መቀነስ ላይ አሰተዋጽኦ ማድረግ እንደሚቻል አንስተዋል፡፡

በኢነርጂ ዘርፍ በተለይ በሃይል ማመንጨት፣ በሃይል ስርጭትና የኢነርጂ መሰረተ ልማት ግንባታ እንዲሁም በከርሰ ምድር ውሃ ቁፋሮ ላይ ባለሃብቶች እንዲሰማሩ ፍላጎት እንዳለም ገልጸዋል፡፡

የቻይና ዓለም አቀፍ ኢነርጂ ቡድን ሊቀመንበር ሉ ዢያንግ በበኩላቸው÷ የቻይና ድርጅቶች በኢትዮጵያ በተለያዩ የልማት ስራዎች ላይ ሲሳተፉ እንደቆዩ አስታውሰዋል፡፡

በቀጣይም በኢነርጂ ልማት ዘርፍ መሰማራት እንደሚፈልጉ ጠቅሰው÷ ወደ ኢንቨስትመንት ለመግባትም ምቹ ሁኔታዎች እንዲመቻቹ መጠየቃቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

በሌላ በኩል የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴዔታ ሡልጣን ወሊ ከጀርመን የልማት ድርጅት (ጂ አይ  ዜድ) ተወካዮች ጋር በኢነርጂ ልማት ትብብር ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡

ኢትዮጵያና ጀርመን የረጅም ጊዜ ግንኙነት እንዳላቸው የገለጹት ኢንጂነር ሡልጣን ወሊ÷ በተለይ የጀርመን የልማት ድርጅት በኢነርጂ ልማት ዘርፍና በሌሎች መስኮች አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የጀርመን የልማት ድርጅት ተወካይ አሌክሳንደር ሃክ በበኩላቸው÷ ተቋማቸው በኢነርጂ ልማት ዘርፍ እያደረገ የሚገኘውን ድጋፍ እንደሚያጠናክር ገልጸዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.