በደቡብ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰተው ድርቅ በዜጎችና እንስሳት ላይ ጉዳት እንዳያደርስ እየተሠራ ነው ተባለ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 28፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ክልል በሚገኙ ዘጠኝ ዞኖችና አራት ልዩ ወረዳዎች ላይ በተከሰተው ድርቅ በዜጎችና እንስሳት ላይ ጉዳት እንዳይደርስ እየተሠራ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለጸ።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ኡስማን ሱሩር ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ ፥ በዝናብ መጠን መቀነስና መቋረጥ ምክንያት ድርቅ ተከስቷል ብለዋል፡፡
የከፋ ድርቅ ያለባቸው ዞኖች ፥ ደቡብ ኦሞ፣ ኮንሶ ዞን እና ቡርጂ፣ አሌ፣ ደራሼ፣ አማሮ ልዩ ወረዳዎች እንደሆኑም ነው ያነሱት፡፡
ድርቁ ያጠቃቸው ሰባት ዞኖች በስምጥ ሸለቆ ውስጥ የሚገኙ ወረዳዎች መሆናቸውንም አስረድተዋል።
ለአብነትም ጎፋ፣ጋሞ፣ ወላይታ፣ ሐዲያ፣ ሐላባ፣ ሥልጤና ጉራጌ ዞን በስምጥ ሸለቆ ውስጥ ያሉ ወረዳዎች ሲሆኑ ፥ የችግሩ ሰለባ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡
በዚህም 342 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የነበረ ሠብል ሙሉ በሙሉና በከፊል በድርቁ መውደሙንም ነው የተናገሩት።
በዞኖቹ በተደረገው ጥናት ከ2 ሚሊየን በላይ ዜጎች የአስቸካይ ጊዜ ዕርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ተረጋግጧል።
ድርቁ በዜጎችና እንስሳት ላይ የከፋ ጉዳት እንዳይደርስም የክልሉ ሥራ አመራር ምክር ቤት የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ድጋፍ ለማቅረብ እየተሠራ መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡
በበላይ ተሥፋዬ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-