Fana: At a Speed of Life!

በአዲስ አበባ የቤት ለቤት የኮሮና ቫይረስ ልየታ ሊጀመር ነው

አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 3 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ከቀጣዩ ሳምንት ጀምሮ በአዲስ አበባ ከተማ የቤት ለቤት የኮሮና ቫይረስ ልየታ እንደሚጀመር አስታወቁ።

ምክትል ከንቲባው ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ በአስተዳደሩ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችን በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም ልየታው በከተማዋ ሁሉም ወረዳዎች በተለይም ተጋላጭ ሊሆኑ ይችላሉ ተብለው በተለዩ ወረዳዎች እንደሚጀመር ተናግረዋል።

ለዚህ እንዲረዳም ጡረታ ላይ የነበሩና በሙያው ልምድ ያላቸው ሃኪሞች ጥሪ ተደርጎላቸዋልም ነው ያሉት።

ምክትል ከንቲባው በመግለጫቸው በከተማዋ አቅም ለሌላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ምግብ የሚያሰባስቡ 1 ሺህ 200 የምግብ ባንኮች መዘጋጀታቸውን ጠቅሰዋል።

እነዚህ የምግብ ባንኮች በከተማዋ ሁሉም ወረዳዎች አቅም ለሌላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ የሚያደርጉ ሲሆን፥ ህብረተሰቡም ለእነዚህ የምግብ ባንኮች ግብአት የሚሆኑ ድጋፎችን እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል።

በተጨማሪም በሚቀጥለው ሳምንት ተማሪዎች ቤታቸው ሆነው ከመምህራኖቻቸው ጋር በጥያቄና መልስ መልክ መረጃ መለዋወጥና መወያየት የሚችሉበት አሰራር ተግባራዊ ይደረጋልም ብለዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ ከ7ኛ ክፍል በታች የሚገኙ ተማሪዎች ትምህርታቸውን በሬዲዮ እንደሚከታታሉ ጠቅሰው፥ ከ7ኛ እስከ 12ኛ ክፍል የሚማሩ ተማሪዎች በመምህራን የተዘጋጁ ትምህርቶችን (በፕሮዳክሽን መልክ) በቴሌቪዥን እንደሚከታተሉ አንስተዋል።

አስተዳደሩ ከኮሮና ቫይረስ ባለፈም መደበኛ ህግ የማስከበርና ሌሎች ስራዎችን እያከናወነ ነው ያሉት ኢንጂነር ታከለ፥ ህክምናው ላይ ከኮሮና ውጭ ያሉ ሌሎች ህመሞችን በመደበኛነት የማከም ስራ እየተሰራ መሆኑንም አውስተዋል።

ከውሃ አቅርቦት ጋር በተያያዘም የተቋማትን የውሃ ፍጆታ እስከ 75 በመቶ በመቀነስ የህብረተሰቡን ፍላጎት ለማሟላት እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።

ከዚህ ባለፈም አሁን ላይ የከተማዋ የምግብ አቅርቦት ከክልሎች የሚገባ እንደመሆኑ መጠን፥ በቀጣይ አስተማማኝ ለማድረግ የከተማ ግብርናን ለማስፋፋት እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

ኢንጂነር ታከለ ኡማ በሆስፒታሎች አሁን ላይ እየታየ ያለውን የደም እጥረት ግምት ውስጥ በማስገባትና የደም ልገሳን ለማበረታታት ደም ለግሰዋል።

በምስክር ስናፍቅ

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.