የተጀመሩ የግንባታ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 29፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የተጀመሩ የግንባታ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቁ በትኩረት እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ዲዛይንና ሱፐርቪዥን ስራዎች ኮርፖሬሽን አስታውቋል፡፡
በኮርፖሬሽኑ የእቅድና ፕሮግራም አስተዳደር ሃላፊ አቢይ ጸጋየ እንደገለጹት፥ ተቋሙ በመንገድ፣ ውሃ እና ህንጻ ፕሮጀክቶች ላይ ደረጃውን የጠበቀ የግንባታ ስራ፣ ቁጥጥር፣ የጥናትና ዲዛይን እንዲሁም የማማከር አገልግሎት እየሰጠ ነው፡፡
ባለፉት ሥድሥት ወራትም 3 ነጥብ 38 ቢሊየን ብር የሚያወጡ 343 አዳዲስ ፕሮጀክቶች ግንባታ ፣ ቁጥጥር፣ ጥናት፣ ዲዛይን እና የማማከር ስራ እያከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በዚህም 934 ሚሊየን ብር ገቢ በማግኘት የእቅዱን 93 ነጥብ 77 በመቶ ማሳካት መቻሉን ነው የገለጹት፡፡
የጸጥታ ችግር፣ የፋይናንስ እጥረት እና የግብዓት ዋጋ መናር ግንባታዎች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ እንዳይጠናቀቁ ያደረጉ ተግዳሮች መሆናቸውንም አንስተዋል፡፡
በተለይም በየጊዜው የሚስተዋለው የግንባታ እቃዎች ዋና ጭማሪ ለፕሮጀክቶች መዘግየት ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚይዝ አስረድተዋል፡፡
የተጀመሩ የግንባታ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ ደረጃቸውን ጠብቀው እንዲጠናቀቁ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡
ለዚህም በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ እና ዘላቂ መፍትሄ ለማበጀት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር ይሰራል ብለዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ