ኢትዮጵያ ስደተኞችን በማስተናገድ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አጋርነቷን አሳይታለች – ተመድ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 29፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ፈተናዎች ቢያጋጥሟትም ስደተኞችን በማስተናገድ ረገድ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አጋርነቷን አሳይታለች ሲል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ገለጸ፡፡
በተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኤጀንሲ የኢትዮጵያ ተወካይ ማማዶ ዲያን ባልዲ ለአልጀዚራ እንደተናገሩት÷ ባለፉት አራት ሳምንታት ውስጥ በሶማሊያ ሶል ግዛት በተፈጠረው ሁከት ሴቶች፣ ህጻናት እና አካል ጉዳተኞች ወደ ኢትዮጵያ ተሰደዋል።
ምንም እንኳ ኢትዮጵያ ችግሮች ቢያጋጥሟትም ከሶማሊያ የመጡ ስደተኞችን በመጠበቅ እና በመንከባከብ ዓለም አቀፋዊ አጋርነቷን አሳይታለች ብለዋል ፡፡
ስደተኞቹ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በሚገኙ 13 መጠለያዎች ውስጥ እንደሚኖሩ የጠቆሙት ተወካዩ÷ በስደተኞች ካምፕ ውስጥ ውሃ፣መጠለያ፣ ጥበቃ፣ትምህርት እና ምግብ ቅደሚያ የሚሰጣቸው አገልገሎቶች መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡
ኢትዮጵያ የራሷ ተግዳሮቶችቢኖሩባትም ዓለም አቀፍ ጥበቃ ለሚያስፈልጋቸው ስደተኞች በሯን ክፍት ማድረጓ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በአርያነት የሚጠቀስ መሆኑን ነው ያሰገነዘቡት፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት፣ የኢትዮጵያ የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች አገልግሎት ፣የተመድ የስደተኞች ኤጀንሲ እንዲሁም ሌሎች የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ አጋሮች ለስደተኞቹ አስቸኳይ አገልግሎቶችን እየሰጡ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
ስደተኞቹ ያረፉበት የሶማሊ ክልል በድርቅ የተጎዳ መሆኑን ያስታወሱት ተወካዩ÷ ስደተኞቹን እና በድርቅ የተጎዱ ማህበረሰቦችን መልሶ ለማቋቋም ጠንካራ ዓለም አቀፋዊ ድጋፍ እንዲደረግ ጠይቀዋል።
ስደተኞቹን በተቻለ ፍጥነት ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ሁኔታዎችን መፍጠር እንደሚያስፈልግም ተወካዩ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡