Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል የአደጋ ስጋት እና የምግብ ዋስትና ችግር ስር እየሰደደ ነው- ዶ/ር ይልቃል ከፋለ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 29፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል የአደጋ ስጋት እና የምግብ ዋስትና ችግር ስር እየሰደደ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ ተናገሩ፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ ዛሬ በጀመረው የክልሉ ምክርቤት መደበኛ ጉባኤ የአስፈፃሚ አካላት የግማሽ በጀት አመት ሪፖርት እያቀረቡ ነው።

ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳሉት ባሳለፍነው ክረምት በጣና ሀይቅ ዙሪያ ባሉ ወረዳዎች መገጭ እና ዓባይ ወንዞች ሞልተው በመውጣት በርካታ መኖሪያ ቤቶችን በመክበብ የሰብል ማሳ እና ማህበራዊ አገልግሎት በጎርፍ ተጥለቅልቀዋል፡፡

በዚህም ከ82 ሺህ በላይ ዜጎች በአደጋ ውስጥ መቆየታቸውን አንስተዋል፡፡

የክልሉ መንግስት ይህን ግምት ውስጥ በማስገባት ከመንግስት በጀት እና ከረጅ ድርጅቶች አጠቃላይ 68 ሚሊየን ብር በመመደብ የጎርፍ መከላከል ስራዎችን እየተገበረ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

ባለፉት ስድስት ወራት በክልሉ አንጻራዊ ሰላም እና መረጋጋት ቢፈጠርም አሁንም ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋትን በመፍጠር በኩል በትኩረት ሊሠራ  ይገባልም ብለዋል፡፡

የዜጎች ሞት እና መፈናቀል ያለመቆሙ አሁንም ከስጋት እና ከችግር እንዳንወጣ አድርጓልም ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፡፡

ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት ለሌሎች የልማት እና የመልካም አሥተዳደር እቅዶች መሳካት ወሳኝ ነው ያሉት ርዕሰ መሥተዳድሩ በሀገርም ሆነ በክልል ደረጃ የገጠሙንን ችግሮች በሠላም እንዲፈቱ በትኩረት ይሠራል ነው ያሉት።

በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ግጭቶች ምክንያት ወደ ክልሉ የመጡ ተፈናቃዮች ቁጥር 576 ሽህ 548 የደረሰ ሲሆን በስድስት ዞን እና በአንድ ከተማ መስተዳድር ውስጥ በ37 ካምፕ እና በማህበረሰቡ ውስጥ ይገኛሉም ነው ያሉት፡፡

በተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ ችግሮች ምክንያት ለአደጋ የተጋለጡ ወገኖችን በፌደራልም እና በክልሉ አቅም ለመደገፍ ጥረት እየተደረገ ቢሆንም በቂ አይደለም ብለዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በሪፖርታቸው ከቡና ልማት ጋር በተያያዘ የወንበራ ቡና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፈላጊና ልዩ ጣዕም ያለው እየሆነ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ ተስፋ ሰጭ መሆኑ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ነው ብለዋል።

በ2015 በጀት ዓመት የቡና ኮሞዲቲ ልማት በስድስት ዞኖች ውስጥ በ19 ወረዳዎች በ152 ቀበሌዎች 2 ነጥብ 7 ሚሊየን የቡና ችግኝ ተከላ መካሄዱን አውስተዋል።

በምንይችል አዘዘው

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.