Fana: At a Speed of Life!

የካርቱም ቀጣናዊ ተልዕኮ ማስፈጸም ማዕከል ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በመከላከል ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተወጣ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 29፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የካርቱም ቀጣናዊ ተልዕኮ ማስፈጸም ማዕከል /ሮክ/ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በጋራ ለመከላከልና ለመዋጋት አይነተኛ ሚና እየተወጣ መሆኑን ኢንተር ፖል ገለጸ፡፡

የሮክ አባል የሆነችው ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ወንጀል ሰርተው የተሰወሩ ወንጀለኞችን በማጋለጥና አሳልፋ ለመስጠት በቁርጠኝነት እየሰራች መሆኑም ተገልጿል፡፡

የካርቱም ቀጣናዊ ተልዕኮ ማስፈጸም ማዕከል /ሮክ/ እንደ አውሮፓውያን የዘመን ቀመር ከ2022 እስከ 2025 የሚተገበረውን የፕሮጀክቱን ሂደት የሚገመግም መድረክ በአዲስ አበባ እያካሄደ መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በአውሮፓ ህብረት 5 ሚሊየን ዩሮ የገንዘብ ድጋፍ የሚንቀሳቀሰው ሮክ በአፍሪካ ህብረት ስር የተቋቋመ ፕሮጀክት ሲሆን÷ ኢትዮጵያን ጨምሮ 11 የአፍሪካ ሀገራት በድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች ላይ በትብብር የሚሰሩበት ነው፡፡

ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርና አዘዋዋሪዎች በዜጎች ላይ የሚፈጽሙትን ሰብዓዊ ጥቃት በተመከለተ መረጃ ለመለዋወጥና አሳልፎ ለመስጠት የሚስችል መሆኑም ተመላክቷል፡፡

የካርቱም ቀጣናዊ ተልዕኮ ማስፈጸም ማዕከል ቴክኒካል ዳይሬክተር ሀርቬ ጃሜት÷ ሮክ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ2019 እስከ 2021 በነበረው የመጀመሪያው ዙር የድርጊት መርሐግብር ከ400 በላይ የወንጀል መረጃዎችን በመሰብሰብ ትንተና ተሰርቶ አስፈላጊው እርምጃ እንዲወሰድ ለዓለም አቀፉ የፖሊስ ተቋም /ኢንተርፖል/ እንዲቀርብ ተደርጓል ብለዋል፡፡

እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2017 ዩሮፖል ባወጣው ሪፖርት መሰረት 5 ነጥብ 7 ቢሊየን ዩሮ በህገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀለኞች መንቀሳቀሱን ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ፣ ግብፅ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ጅቡቲ፣ ኤርትራ፣ ኬንያ፣ ሊቢያ፣ ቱኒዚያ፣ ዩጋንዳና ሶማሊያ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በጋራ በመከላከል ተጨባጭ ለውጥ አምጥተዋል ብለዋል፡፡

እስካሁንም በሮክ አማካኝነት ከ700 በላይ የወንጀል መረጃዎችን በመሰብሰብ አባል ሀገራት በጋራ እንዲከላከሉ ለማስቻል መረጃ ለኢንተርፖል ማድረሳቸውን ገልጸዋል፡፡

ሮክ የፕሮጀክቱ ሁለተኛ ዙር መርሐ ግብር ይፋ ከሆነበት ግንቦት 2022 ጀምሮ ከኢንተርፖልና ከአባል ሀገራት ጋር በመተባበር ከ2 ሺህ 200 በላይ ተጎጅዎችን ከህገ ወጥ አዘዋዋሪዎች ማስለቀቅ ተችሏል ነው ያሉት፡፡

የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ትብብር ድርጅት ዋና ስራ አስፈፃሚና የኢንተርፖር ቀጣናዊ ቢሮ ሊቀ-መንበር ጌዲዮን ኪሚሊ÷ ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች አባል ሀገራት ለፕሮጀክቱ መሳካት የነቃ ተሳትፎ እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ በህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር በኢንተርፖል የሚፈለጉ ወንጀለኞችን ጭምር አጋልጦ በመስጠት በቀጣናው ያለውን ህገ-ወጥ እንቅስቃሴ ለመግታት የሚደረገውን ጥረት እያገዘች መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

የሜዲትራኒያን አካባቢ ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ሌሎችም ዓለም አቀፍ ወንጀሎች የሚፈጸሙበት ቀጣና መሆኑን የገለጹት ሊቀመንበሩ÷ ከሊቢያና ደቡብ አፍሪካ ሸሽተው የሚመጡ ወንጀለኞችን አሳልፋ መስጠቷንም ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የወንጀል ምርምራ ቢሮ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል ዘላለም መንግስቴ÷ በአውሮፓና በሌሎች ሀገራት በኢንተርፖል የመያዣ ትዕዛዝ የወጣባቸው ህገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችን አሳልፈን ሰጥተናል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ የሮክ አባል በመሆኗ ዓለም አቀፍ ወንጀል ሰርተው የተሰወሩ አካላትን በማጋለጥና አሳልፋ ለመስጠት በቁርጠኝነት እየሰራች መሆኑን ጠቅሰው÷ ሮክ ማስተባበሪያ ቢሮውን በአዲስ አበባ እንዲከፍትም ጥያቄ አቅርበናል ብለዋል፡፡

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.