ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ ሊቀመንበርነትን ከኬንያ ተረከበች
አዲስ አበባ፣ የካቲት 29፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ ሊቀመንበርነትን ዛሬ ከኬንያ ተረከበች፡፡
የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት የገንዘብ ሚኒስትሮች ስብሰባ ዛሬ በናይሮቢ የተካሄደ ሲሆን÷ ባለፈው ዓመት በአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ የተከናወኑ ስራዎችን ገምግመዋል፡፡
በግሉ ዘርፍ ተሳትፎ እና በዲጂታል ትስስር ቀጣናዊ ውህደትን ማሳደግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይም መክረዋል፡፡
በተጨማሪም በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና የተከሰተውን የአየር ንብረት ለውጥ እና ያስከተላቸውን ጉዳቶች እንዲሁም በሌሎች ጉዳዮች ላይ መወያየታቸውን የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡
ስብሰባውን የተካፈሉት የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሺዴ÷ በቀጣናው ቆላማ አካባቢዎች የተከሰተውን የድርቅ አደጋ ለመከላከል በውሃ፣ በግብርና እና በእንስሳት ሀብት ዘርፍ የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ለማስቀጠል የገንዘብ ድጋፍ ያደረጉ አጋር አካላትን አመስግነዋል፡፡
በቀጣናው ጥልቅ የኢኮኖሚ ውህደትን ለመገንባት የሀገራቱ ድጋፍ እና አጋርነት አስፈላጊ መሆኑንም ነው በአጽንኦት የገለጹት፡፡
በስብሰባው ማጠናቀቂያ ላይም ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ ሊቀመንበርነትን ከኬንያ የተረከበች ሲሆን÷ አቶ አህመድ ሺዴ የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭን በቀጣይ በሊቀመንበርነት ይመራሉ፡፡