በደቡብ ክልል ለአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት በቂ መጻሕፍት ማቅረብ አልተቻለም ተባለ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 29፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በበጀት እጥረት ምክንያት ለአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት የሚያገለግሉ በቂ መጻሕፍት አሳትሞ ማቅረብ አለመቻሉን የደቡብ ክልል ትምህርት ቢሮ ገለጸ፡፡
በወላይታ እና ጉራጌ ዞኖች የአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት መጻሕፍት ባለማግኘታቸው በመማር ማስተማር ሂደቱ ላይ ዕክል ፈጥሮብናል ሲሉ መምህራንና ተማሪዎች ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡
ተማሪዎቹ መጻሕፍቱ ስለሌላቸው ለክልል አቀፍ እና ሀገራዊ ፈተናዎች ለመዘጋጀት መቸገራቸውንም ነው የገለጹት፡፡
በደቡብ ክልል ትምህርት ቢሮ የሥርዓተ ትምህርት ዝግጅት እና ትግበራ ዳይሬክተር እንዳሻው ይስማ÷ በበጀት እጥረት ምክንያት ለአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት መጻሕፍት ማሳተም አለመቻሉን ጠቁመዋል፡፡
ሀገር አቀፍ ፈተና ለሚወስዱ የክልሉ 8ኛ ክፍል ተማሪዎች 1 መጽሐፍ ለአምስት ተማሪዎች መሰጠቱንም ጠቅሰዋል፡፡
ክልሉ መጻሕፍት አሳትሞ ማከፋፈል የሚችለው በ2016 የትምህርት ዘመን መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
በሲሳይ ዱላ