ዓለምአቀፋዊ ዜና

ሩሲያ በዩክሬን ከተሞች የሚሳኤል ጥቃት መፈጸሟን የዩክሬን ባለስልጣናት ገለጹ

By Alemayehu Geremew

March 09, 2023

አዲስ አበባ፣ የካቲት 30፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሩሲያ በዩክሬን የተለያዩ ከተሞች ላይ የሚሳኤል ጥቃት መፈጸሟን የዩክሬን ባለስልጣናት ገለጹ፡፡

አሁን ላይ የዩክሬንን ዋና ከተማ ኪየቭን ጨምሮ ጥቁር ባሕር ፣ የኦዴሳ ወደብ እና የሰሜን ምሥራቅ ካርኪቭ ከተማ በሚሳኤል መመታታቸውን የአካባቢዎቹ ባለሥልጣናት አስታውቀዋል፡፡

የሚሳኤል ጥቃቱ በኦዴሳ የሚገኘውን የኃይል ተቋም ማውደሙንም አልጀዚራ ዘግቧል፡፡

በካርኪቭ ወሳኝ የመሠረተ ልማት አውታሮች መመታታቸውን የጠቆሙት የከተማዋ ከንቲባ ኢሆር ቴሬኮቭ ናቸው፡፡

በከተማዋ አንዳንድ አካባቢዎች የኤሌክትሪክ አገልግሎት መቋረጡንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

የኪየቭ ከተማ ከንቲባ ቪታሊ ክሊችኮ ÷ በደቡባዊ ሆሎሲቪስኪ ፍንዳታ መድረሱን ጠቁመው ለአካባቢው ነዋሪዎች ድጋፍ ለማድረስ እና መሠረታዊ አገልግሎቶችን ለመሥጠት ሁሉም ትኩረቱን ወደዛው ማድረጉን አስረድተዋል፡፡

ከሩሲያ በኩል የተወነጨፉ 15 ሚሳኤሎች በዩክሬን ምሥራቃዊ ክፍል በምትገኘዋ ካርኪቭ እና ወጣ ብሎ በሚገኝ አካባቢ የመኖሪያ ኅንፃዎችን ማውደማቸውን የአካባቢው ገዢ ኦሌህ ሲኒዬሁቦቭ ተናግረዋል።

በጥቃቱ እስካሁን ለህልፈት የተዳረገ ሰው አለመኖሩንም ዘገባው አመላክቷል።