በፍትሕ ሚኒስቴር የድሬዳዋ ቅርጫፍ የዓቃቤ ሕግ ጽ/ቤት ኃላፊ ከቀረበባቸው የሙስና ክስ ነጻ ተባሉ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 30፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በፍትህ ሚኒስቴር የድሬዳዋ ቅርጫፍ የዓቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ፈይሳ ሾርኬ ከቀረበባቸው ተደራራቢ የሙስና ወንጀል ክስ ነጻ ተባሉ፡፡
ብይኑን የሰጠው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው።
ተከሳሹ በድሬዳዋ ከተማ ቀበሌ 03 የሚገኝ ሆቴል በሙስና ምርመራ በፍርድ ቤት የታገደባቸውን እግድ አስነሳለሁ በማለት ከሌሎች ግብረአበሮች ጋር ሆነው ሕዳር 30 ቀን 2014 ዓ.ም የግል ተበዳዩ 15 ሚሊየን ብር ጉቦ እንዲከፍሉ ጫና ፈጥረዋል በሚል ተከሰው ነበር፡፡
እንዲሁም በወንጀል የተገኘ ገንዘብን (ንብረትን) ሕጋዊ አድርጎ በማቅረብ ወንጀል ሌላ ክስ ቀርቦባቸው እንደነበር ይታወሳል፡፡
በአጠቃላይ ግለሰቡ ባሳለፍነው ዓመት በከባድ የሙስና ወንጀል ክስ እንደቀረበባቸው ይታወቃል፡፡
ተከሳሹ ክሱ ከተነበበላቸው በኋላ ወንጀሉን አለመፈጸማቸውን ገልጸው የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡
እንዲሁም ዓቃቤ ሕግ ለወንጀሉ መፈጸም የሚያስረዱ ሥድስት ምስክሮችን ቃል አሰምቷል።
ፍርድ ቤቱም የምስክሮችን ቃል መርምሮ በዛሬው ቀጠሮ የተሰሙ ምስክሮች ተከሳሹ ወንጀሉን ለመፈጸሙ አላስረዱም ሲል አብራርቷል።
ስለሆነም የተጠቀሱ የወንጀል ድርጊቶችን ተከሳሹ መፈጸማቸው ባለመረጋገጡ ነጻ ነው ሲል ፍርድ ቤቱ ብይን ሰጥቷል።
በታሪክ አዱኛ