ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች የእናቶችና ሕጻናትን ጤና አገልግሎት ለማሻሻል የአጋር አካላት ሚና ወሳኝ ነው ተባለ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 30፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎች ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች የእናቶች እና ሕጻናትን ጤና አገልግሎት ለማሻሻል የአጋር አካላት ሚና ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ።
የተዋልዶ ጤና አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ህብረት 3ኛው ዓመታዊ ጉባዔ የተለያዩ ሀገራት ተወካዮች ባተገኙበት በአዲስ አበባ ከተማ ተካሂዷል።
ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በእናቶች፣ በሕጻናትና በወጣቶች እንዲሁም ስነ-ተዋልዶ ጤና አገልግሎት መስኮች አበረታች ውጤት ማስመዝገቧን የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
በጉባዔው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የጤና ሚኒስትር ዴዔታ አማካሪ ፕሮፌሰር ስለሺ ጋሩማ÷ ኢትዮዮጵያ የእናቶችና ሕጻናት ጤና አገልግሎትን ለማሻሻል በፖሊሲና በስትራቴጂ ላይ የተመሰረቱ ተግባራትን በማከናወኗ ችግሩን መቀነስ ችላለች ብለዋል።
ካለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ወዲህ የእናቶችና ሕጻናት ሞት ከ70 በመቶ በላይ መቀነስ መቻሉን ጠቅሰው÷ የጤና ተቋማት መስፋፋት፣ የአገልግሎት ተደራሽነት ማደግና የስነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎት መስፋፋት ለተገኙት ውጤቶች ጉልህ ሚና ማበርከታቸውን ገልጸዋል።
እንደ ኮሮና፣ የሰሜኑ ግጭት፣ ድርቅ እና ጎርፍ እንዲሁም ሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ አደጋዎች በኢትዮዮጵያ ጤና ልማት ዘርፉ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ያሳደሩ መሆናቸውንም አንስተዋል፡፡
ይሁን እንጂ በሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎች በተጎዱ አካባቢዎች የእናቶች፣ የህጻናት እና የስነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎትን ለማጠናከር የአጋር አካላት ሚና ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮዮጵያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየተገበረችው ያለው የጤና መድን ስርዓት የውስጥ አቅምን በማጠናከር ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝም ነው የገለጹት፡፡
ትብብርን ማጠናከር የጤና ስርዓትን ተደራሽነትና ጥራት ለማሻሻል አስፈላጊ መሆኑን አውስተው÷ የተዋልዶ ጤና አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ህብረት 3ኛው ዓመታዊ ጉባዔ በዚህ ረገድ አይነተኛ ጠቀሜታ አለው ነው ያሉት፡፡
የተዋልዶ ጤና አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ህብረት ዋና ዳይሬክተር አበበ ከበደ በበኩላቸው÷ ማህበሩ በስነ ተዋልዶ ጤና ዙሪያ በተናጠል ይከናወኑ የነበሩ ተግባራትን በተደራጀ መልኩ ለመምራትና የመንግስትን ግቦችን ለማሳካት የሚያስችሉ የተቀናጁ ተግባራትን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት የልማት ጉዳይ መሆኑን ገልጸው÷መንግስ የሚያወጣቸው ፖሊሲዎች እና እቅዶች በሲቪል ማህበራት እንዲተገበሩ ለማድረግና እና ለዚህም አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶች እንዲሟሉ ማህበሩ ጥረት እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
በወንደሰን አረጋኸኝ