Fana: At a Speed of Life!

ብሔራዊ የአደጋ ሥጋት አመራር ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ አካሄደ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 30፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ሰብሳቢነት ብሔራዊ የአደጋ ሥጋት አመራር ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባውን አካሂዷል፡፡

በዋነኛነት በአየር ሁኔታ መዛባት ምክንያት ባለፉት 5 የዝናብ ወቅቶች በኢትዮጵያ አንዳንድ ክፍሎች ከፍተኛ የዝናብ እጥረት መከሰቱ ተመላክቷል፡፡

በተለይም በደቡባዊ፣ ደቡብ ምሥራቅ እና ደቡብ ምዕራብ ክፍሎች የዓየር መዛባቱ ድርቅ እንዳስከተለና ዘርፈ ብዙ ጉዳት ማድረሱ ተጠቁሟል፡፡

የፌዴራል መንግሥት እና ክልሎች ከሕዝብ እና ከአጋር ተቋማት ጋር በመሆን ለችግሩ ተገቢ ምላሽ ለመስጠት ከፍተኛ ጥረት መደረጉ ነው የተገለጸው፡፡

በሌላ በኩል በሰው ሰራሽ አደጋዎች መንስኤነት ተፈናቅለው የሚገኙ ዜጎች ጉዳይ ከፍተኛ ትኩረትን የጠየቀ ስራ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

በዛሬው ዕለትም በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ሰብሳቢነት ብሔራዊ የአደጋ ሥጋት አመራር ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባውን አካሂዷል፡፡

ምክር ቤቱ የድርቁን ዝርዝር ሁኔታ፣ የደርሰውን የጉዳት መጠን፣ የተከናወኑ የአደጋ ምላሽ ሥራዎችን የሚያሳዩ ሪፖርቶችን በሚገባ ገምግሟል፡፡

ከዚህ ባለፈም ጥንካሬዎች እና ጉድለቶችን መለየቱን ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በአጭር እና በረጅም ጊዜ ሊከናወኑ የሚገባቸውን የአደጋ ምላሽ እና የዘላቂ ልማት ሥራዎች በመለየት በቅንጅትና በርብርብ ለመተግበር አቅጣጫ መቀመጡም ተጠቁሟል፡፡

ምክር ቤቱ በመጪዎቹ አራት ወራት በልዩ ትኩረት ቅድሚያ ተሠጥቷቸው የሚሰሩ ሥራዎችን የለየ ሲሆን÷ ፈጣን ምላሸ ለመስጠት ሥራዎችን በቅርበት እየገመገመ እንደሚሠራም አስታውቋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.