የቀድሞ ተዋጊዎች የመልሶ ማቋቋሚያ መርሐ ግብር ላይ የሚመክር ውይይት በመቀሌ እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 1 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌዴሪ ብሄራዊ የተሃድሶ ኮሚሽን ከባለድርሻ እና አጋር አካላት ጋር የቀድሞ ተዋጊዎችን የመልሶ ማቋቋም ሂደት ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ በመቀሌ እያካሄደ ነው።
የብሄራዊ የተሃድሶ ኮሚሽነር አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ÷ የጋራ የምክክር መድረኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በመቀሌ እንዲካሄድ የተደረገበት ዋናው ዓላማ ከተኩስ አቁም ስምምነት በኋላ በክልሉ የተረጋጋ ሁኔታ በመኖሩ ነው ብለዋል፡፡
በተጨማሪም በሁለቱ ተስማሚዎች መካከል መተማመን መጎልበቱን ማሳያ እንዲሆን ታስቦ የተደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ኮሚሽነሩ ከተዋጊነት የሚሰናበቱ የቀድሞ ተዋጊዎችን ከማህበረሰቡ ጋር በዘላቂነት እንዲቀላቀሉ እና በልማት፣ በሰላምና በዴሞክራሲ ግንባታ ውስጥ እንዲሳተፉ እንዲሁም በዘላቂነት ወደ ሰላማዊ ኑሮ እንዲመለሱ እንደሚሰራም አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት ሁለት ጊዜ የተሃድሶ መርሐ ግብር ማካሄዷን ያስታወሱት አምባሳደር ተሾመ ÷ካለፉት እና ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን በመውሰድ የአሁኑን የተሃድሶ መርሐ ግብር ውጤታማ ለማድረግ እንደሚሰራም ነው የተናገሩት።
አቶ ጌታቸው ረዳ በበኩላቸው ÷ የሚደረገው ምክክር ሰላሙን ለማጠናከርና ወደፊት ለሚደረገው የመልሶ ግንባታ እና የተሃድሶ ስራ ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው ጠቅሰዋል።
የሙያ ዘርፋቸውን በመተው በውጊያ ላይ የነበሩ ተዋጊዎችን ወደ ቀደመ የሙያ ዘርፋቸው እንዲመለሱ ማድረግ እንደሚገባም አንስተዋል።
አቶ ጌታቸው የሚደረገው ውይይት ለትግራይ ብቻ ሳይሆን በሀገር ደረጃ የመልሶ ግንባታና የተሃድሶ ስራው ምን መምሰል አለበት የሚለውን ለማሳየትም አጋዥ መሆኑንም ነው የተናገሩት።
መርሐ ግብሩ ስኬታማ እንዲሆን ድጋፍ እያደረገ የሚገኘው የተባበሩት መንግስታት የልማት መርሐ ግብር ኃላፊ ቱርሃን ሳላ÷ ከኢትዮጵያ ጋር መቆም የሁሉም ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ኃላፊነት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅ በሁሉም ዘርፍ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላልም ብለዋል።
የተሃድሶ መርሐ ግብርሩ የቀድሞ ተዋጊዎችን ወደ ማህበረሰቡ እንዲቀላቀሉ እና በበጎ መልኩ አስተዋጽኦ እንዲያበረከቱ እንደሚያስችላቸውም ጠቅሰዋል።
በዘመን በየነ