እስራኤል የመንገደኞችን አውሮፕላን ወደ ጭነት አገልግሎት የመቀየር ስራ እንደምትደግፍ ገለጸች
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 1፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) እስራኤል የኢትዮጵያ አየር መንገድ የመንገደኞችን አውሮፕላን ወደ ጭነት አገልግሎት ለመቀየር የሚያደርገው ጥረት እንደምትደግፍ አስታወቀች፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፋጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው በኢትዮጵያ ከእስራኤል አምባሳደር አለልኝ አድማሱ ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም የኢትዮጵያ አየር መንገድ የመንገደኞችን አውሮፕላን ወደ ጭነት አገልግሎት ለመቀየር የሚያደርገው ጥረት ማሳደግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡
አምባሳደር አለልኝ በቀጣይ በኢትዮጵያ የ“ኤሮስፔስ ኢንደስትሪ ማዕከል”በመክፈት ተማሪዎችን በዘርፉ ለማሰልጠን እቅድ መያዙን ተናግረዋል፡፡
አቶ መስፍን ጣሰው በበኩላቸው 3ኛው የመንገደኞች አውሮፕላንን ወደ ጭነት አገልግሎት የመቀየር ሒደት በመገጣጣሚያ እቃዎች እጥረት መዘግየቱን ተናግረዋል፡፡
አየር መንገዱ ከመንገደኞች አውሮፕላን ወደ ጭነት አገልግሎት የምትቀየረውን 3ኛ አውሮፕላን በሚቀጥለው ወር እንደሚያጠናቅቅ መናገራቸውንም ከኤምባሲው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በቅርቡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከእስራኤሉ “ኤሮስፔስ ኢንደስትሪ” ጋር በመተባበር የመንገደኞች አውሮፕላንን ወደ ጭነት አገልግሎት መቀየሩ የሚታወስ ነው፡፡