ኢትዮጵያና ጃፓን የ25 ነጥብ 4 ሚሊየን ዶላር የድጋፍ ስምምነት ተፈራረሙ
አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 1 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያና ጃፓን ለመጠጥ ውሀ ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያና ለማዳበሪያ ግዢ የሚውል የ25 ነጥብ 4 ሚሊየን ዶላር የድጋፍ ስምምነት ተፈራረሙ።
ስምምነቱን የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሰመሪታ ሰዋሰው እና በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ኢቶ ታካኮ ፈርመውታል፡፡
ከድጋፉ ውስጥ 19 ነጥብ 2 ሚሊየን ዶላሩ ለአነስተኛ ከተሞች ለመጠጥ ውሀ ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ እንደሚውል የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል።
4 ነጥብ 8 ሚሊየን ዶላሩ ደግሞ 2 ሺህ 500 ሜትሪክ ቶን የአፈር ማዳበሪያ ግዢ ለመፈጸም የሚውል መሆኑ ታውቋል፡፡
በመጠጥ ውሀ ፕሮጀክቱ በትናንሽና በገጠር ከተሞች የሚኖሩ ከ47 ሺህ በላይ ቤተሰቦች ተጠቃሚ ይሆናሉ ነው የተባለው።
የአፈር ማዳበሪያ ድጋፉ ደግሞ በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተውን የአፈር ማዳበሪያ የዋጋ ንረት በመጠኑ ለማረጋጋት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ታምኖበታል፡፡