የሀገር ውስጥ ዜና

ዜጎች በየከተሞቹ በሚፈጠሩ የምክክር መድረኮች  ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀረበ

By ዮሐንስ ደርበው

March 11, 2023

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 2፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሠ ቱሉ ሁሉም ዜጋ በየከተሞቹ በሚፈጠሩ የምክክር መድረኮች በመገኘት ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ዶክተር ለገሠ ቱሉ  ሁሉን አቀፍ የሽግግር ፍትኅ ሂደቱ ስኬታማ እንዲሆን ÷ አሳታፊ፣ ተጎጂዎችን ማዕከል ያደረገ፣ የዓለም አቀፍ ልምዶችንና መርኅዎችን ያከበረ ብሎም የሀገራችንን ነባራዊ ሁኔታ መሠረት ባደረገ የፖሊሲ ማዕቀፍ መምራት ይገባል ብለዋል፡፡

ለዚህም የሽግግር ፍትኅ የፖሊሲ ማዕቀፍ አማራጮችን የሚያመለክት ረቂቅ ሠነድ በፍትኅ ሚኒስቴር በኩል ተዘጋጅቶ ለህዝብ ውይይት መቅረቡን ጠቁመዋል፡፡

በቀረቡ አማራጮች ላይ ተመሳሳይ የዓላማ አንድነት እና አረዳድ ለመፍጠር ብሎም ግብዓት ለመሰብሰብ በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ ከሃምሳ ባላይ ከተሞች ምክክሮች ማካሄድ መጀመሩን አስታውቀዋል፡፡

ለሰብዓዊ መብቶች መከበርና ለሕግ የበላይነት መረጋገጥ የሽግግር ፍትኅ ሥርዓትን መተግበር እንደሚያሥፈልግ እና እጅግ ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንዳለውም ነው ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው የገለጹት፡፡

በሀገራችን በተለያዩ ጊዜያት የተፈጸሙ ጉልኅ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችና ቁርሾዎች አግባብነት ባለው ሁኔታ መፈታት እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ያለችበት አውድ ሁለንተናዊ የተቀናጀና አሳታፊ የሽግግር ፍትኅ ሂደት ዕውን እንዲሆን ግድ የሚልበት መሆኑንም ነው ያመላከቱት፡፡ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ  ጉልኅ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፣ በደሎች፣ ዝንፈቶች፣ ቁርሾዎችና ኢ-ፍትሃዊነቶች  መፈጸማቸውንም አስታውሰዋል፡፡ እውነትን፣ ፍትኅን፣ ሠላምንና እርቅን መሠረት ባደረገ መልኩ ለመፍታትም ሁሉን አቀፍ የሽግግር ፍትኅ ሥልት መከተል እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

ሁሉን አቀፍ የሽግግር ፍትኅ ለዘላቂ ሠላም ግንባታ፣ ለዘላቂ ልማት፣ ለማኅበራዊ ትሥሥርና ለሀገረ መንግስት ግንባታ ሚናዊ አይተኬ ነው ሲሉም ነው የገለጹት፡፡

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/ ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!