ሕጋዊ የወርቅ ፈቃዳቸውን እንደ ሽፋን ተጠቅመው ሕጉን በጣሱ አካላት ላይ እርምጃ ተወሰደ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 2፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በጋምቤላ ክልል በመንግሥት የተሰጣቸው ሕጋዊ የወርቅ ፈቃድ እንደ ሽፋን በመጠቀም ሕጉን ጥሰዋል በተባሉ አካላት ላይ እርምጃ መወሰዱ ተገለጸ፡፡
የዲማ ወረዳ የወርቅ ቁጥጥር ኮማንድ ፖስት ÷ የክልልና የዞን የማዕድን ሴክተር ኃላፊዎች በተገኙበት ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ በወርቅ ዙሪያ ያጋጠሙ ችግሮችን በዝርዝር ገምግሟል፡፡
በግምገማውም በዲማ ወረዳ የወርቅ ምርት ቢኖርም ሌብነትና ኅገወጥነት በመበራከቱ ወርቁ ወደ ብሔራዊ ባንክ በተፈለገው አግባብ እየገባ እንዳልሆነ ተገልጿል፡፡
በመሆኑም በወረዳው ወርቅ እንዲያመርቱ የተሰጣቸውን ፈቃድ እንደ ሽፋን ተጠቅመው ያመረቱትን ወርቅ ወደ ብሔራዊ ባንክ ከመላክ ይልቅ በሕገ-ወጥ መንገድ ወርቁን የማሸሽና የመደበቅ ተግባር በተደጋጋሚ መፈፀማቸውን ተከትሎ ኮማንድ ፖስቱ ቀጥሎ የቀረበውን ውሳኔ አሳልፏል፡፡
በወረዳው ከሚሰሩ 47 ልዩ አንስተኛ የወርቅ አምራቾች ውስጥ 36 ከዛሬ ጀምሮ የተሰጣቸው ፈቃድ ተሰርዞ ከስራው እንዲሰናበቱ እንዲሁም በወረዳው ከሚገኙት 34 በወርቅ ግብይት ማዕከል ከሚሠሩት መካከል 33 ከዛሬ ጀምሮ ፈቃዳቸው ተሰርዞ ከስራ እንዲሠናበቱ ተወስኗል፡፡
እንዲሁም በወረዳው የወርቅ የድንጋይ ወፍጮዎች የመጨረሻ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ እንዲሠጣቸው እና አጠቃላይ የእጅ የወርቅ መመርመሪያ ማሽኖች ወደ ማዕከል ተሰብስበው እንደ አዲስ በአግባቡ በሕግ እንዲመዘገቡ ውሳኔ ተላልፏል፡፡
በተጨማሪም ኮማንድ ፖስቱ በወረዳው በወርቅ ስራ የተሰማሩ ከ21 የውጭ ዜጎች መካከል 18 የተሰጣቸው ፈቃድ ተሰርዞ እንዲባረሩ ወስኗል፡፡
በሌላ በኩል በወረዳው ውስጥ የሚመረተውን ወርቅ በሕጋዊ አግባብ ብቻ ወደ ብሔራዊ ባንክ እንዲገባ ለማድረግ ጥብቅ ክትትል እንዲደረግ አቅጣጫ መቀመጡን ከጋምቤላ ክልል ፕሬስ ሴክሬታሪያት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!