ጤናማ የንግድ ሥርዓት ሊዘረጋ እንደሚገባ ተመለከተ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 2፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ የተጋነነ ዋጋ በማቅረብ ሸማቹን የሚያማርሩ ነጋዴዎችን መቆጣጠር አለበት ሲሉ አቶ ግርማ የሽጥላ ተናገሩ፡፡
የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ውይይት እያካሄደ ነው፡፡
የአማራ ክልል የብልፅግና ፓርቲ ጽሕት ቤት ኃላፊ ግርማ የሽጥላ በውይይቱ ላይ እንደተናገሩት÷ ሥግብግብ ነጋዴዎች እና ደላላዎች ተመሳጥረው አምራቹን ማኅበረሰብ ተጠቃሚ የማያደርግ ሥርዓት እየዘረጉ ወዳልተፈለገ መንገድ እንድንሄድ ሊያደርጉን አይገባም ብለዋል፡፡
የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮም በገበያ ሥርዓት የሚመራ የንግድ እና ግብይት ሥርዓት መፍጠር አለበት ብለዋል፡፡
በነፃ ገበያው የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ ወዳልተፈለገ መንገድ በመጠምዘዝ ሕገወጥነትን እንደ ሕጋዊነት ለመውሰድ የሚፍጨረጨርን አካል ማስቆም ይገባል ማለታቸውን አሚኮ ዘግቧል፡፡