የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማስፈጸም በተዘጋጀው ረቂቅ ደንብ ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ
አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 3 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) 82ኛ መደበኛ ስብሰባውን ያካሄደው የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማስፈጸም በተዘጋጀው ረቂቅ ደንብ ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ።
ምክር ቤቱ በስብሰባው በአሁኑ ጊዜ በአለም አ ቀፍ ደረጃ ኮቪድ-19 በወረርሽ ደረጃ በከፍተኛ ሁኔታ በመስፋፋት በሰው ህይወት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ እንደሚገኝ በማንሳት የተለያዩ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ ጉዳቶችን እያደረሰ እንደሚገኝ ተመልክቷል፡፡
ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ የመጣው ይህ የቫይረሱ ስርጭት በሰዎች ጤናና ህይወት እያስከተለ ካለው መጠነ ሰፊ ጉዳት አንጻር በተለመደው የመንግስት መደበኛ አሰራር መቆጣጠር ወደ ማይቻልበት ደረጃ ተደርሷል ነው ያለው፡፡
በመሆኑም ይህን ሁኔታ በቁጥጥር ስር ለማድረግና የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ ብሎም ለማስወገድ የሚኒስተሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በ30/7/2012 ዓም አውጇል፡፡
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጸደቀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መሰረታዊ የሚባሉ ጉዳዮችን የያዘ ሲሆን ዝርዝር ጉዳዮች በተለይም ስለሚደረጉ የመብት እገዳዎችና ክልከላዎች እንዲሁም መሰል ተግባራት በሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚወጣ ደንብ እንደሚወሰን ከመደንገጉም በላይ የህገ-መንግስቱ ድንጋጌ አንቀፅ 93/4/ም የሚኒስትሮች ምክር ቤት ዝርዝር ደንብ እንደሚያወጣ ተደንግጓል፡፡
በእነዚህ ህጋዊ መነሻዎች አግባብ የኮቪድ-19 ሥርጭትን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠር እና የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ የወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር 3/2012 ማስፈፀሚያ ደንብ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ ጥልቅ ውይይት ከተደረገበት በኋላ አንዳንድ ማስተካከያዎችን በማከል በሙሉ ድምጽ አፅድቆታል።