Fana: At a Speed of Life!

በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የጨረር ህክምና ወረፋ መብዛት ለተጨማሪ የጤና እክል እየዳረጋቸው መሆኑን ታካሚዎች ገለጹ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 2፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በጥቁር አንበሳ አጠቃላይ ሆስፒታል የጨረር ህክምና ወረፋን እየጠበቁ ያሉ ታካሚዎች ለተጨማሪ የጤና እክል እየተዳረግን ነው ሲሉ ቅሬታቸውን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ገለጹ፡፡

በሆስፒታሉ የጨረር ህክምና አንዱ የካንሰር ህክምና ሆኖ በመሰጠት ላይ ይገኛል።

በሆስፒታሉ ሁለት የህክምና ማሽን ብቻ አገልግሎት እየሰጠ በመሆኑ ታካሚዎች ወረፋ በመጠበቅ ለተጨማሪ የጤና እክልና እንግልት እንዲሁም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እየተዳረጉ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

የህክምና አገልግሎቱን ለመጠቀም ታካሚዎች ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች በመዲናዋ ይከትማሉ፡፡

አስተያታቸውን የሰጡን አስታማሚዎች ለህክምና በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ለአመታት መመላለሳቸውን ነው የሚናገሩት።

የቤተሰብ አባሏን ለማሳከም በሆስፒታሉ ያገኘናት ወጣትም፥ ታካሚው የካንሰር የጨረር ህክምና መውሰድ እንዳለበት ከተነገረው ሁለት ዓመት ቢያልፈውም እስካሁን በወረፋ ምክንያት ህክምናውን ማግኘት እንዳልቻለ ትገልጻለች።

ህክምና በጊዜ ማግኘት ባለመቻሉ ምክንያትም በአንድ በኩል ያለው የፊት ክፍሉ መንቀሳቀስ እንደማይችልና ስሜት አልባ እንደሆነም በሀዘኔታ ትናገራለች፡፡

ጣቢያችን በሆስፒታሉ ተገኝቶ ባደረገው ምልከታ እና ታካሚዎችን ባነጋገረበት ወቅት ፥ ከዓመት በላይ እየጠበቁ ያሉ ታካሚዎች መኖራቸውን ታዝቧል።

ካንሰር በባህሪው ከአንዱ አካል ወደሌላው የአካል ክፍል በመሰራጨት ጉዳቱን እያሰፋ እንደሚሄድ የሚጠቅሱት የህክምና ባለሙያዎች፥ በጊዜ ህመሙን በማወቅ የካንሰር ህዋሶች በዚያው ቦታ እንዳሉ ለማጥፋትና የካንሰሩን እድገት በጨረር ህክምና ማገድ እንደዋነኛ ምርጫ ይጠቀሙታል፡፡

በዚህም የጨረር ህክምና ተመራጭ ቢሆንም ፥ በኢትዮጵያ የጨረር ህክምና አገልግሎት የሚሠጡት ጥቁር አንበሳን ጨምሮ ጅማ እና ሃሮማያ ሆስፒታሎች ብቻ ናቸው፡፡

በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የካንሰር ህክምና ክፍል ኃላፊ እና የካንሰር ህክምና ስፔሻሊስት ዶክተር ኤዶም ሰይፈ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ ፥ በሆስፒታሉ ሁለት የጨረር ህክምና ማሽን እንዳሉ አንስተዋል፡፡

እነዚህም የ”ኮባልት” ማሽንና በቅርብ ጊዜ የተገጠመው የ”ሊነር አክሲሌረተር” የተባለ የጨረር ማሽኖች ናቸው፡፡

ይሁን እንጂ ማሽኖቹ በአገልግሎትና በተለያዩ ምክንያቶች ብልሽት ስለሚያጋጥማቸውም ካለው የታካሚ ብዛት ጋር ተዳምሮ በህክምና አሰጣጡ ላይ ችግር መፍጠሩም ይነገራል።

ማሽኖቹ ተከታታይ የሆነ ጥገና የሚፈልጉና ጥቃቅን የሚባሉ የሶፍትዌር፣ የሃርድዌር፣ ጥገና፣ ቁሳቁስ አለማግኘትና በመሰል ችግሮች ምክንያት ለብልሽት እንደሚዳረጉም ነው የገለጹት።

በሆስፒታሉ አሁን ላይ እየሰሩ ካሉት ሁለት የጨረር ህክምና ማሽኖች ካለው ፍላጎት ጋር የሚመጣጠኑ እንዳልሆኑም ያስረዳሉ፡፡

በዚህም የጨረር ህክምና ማሽኖች በተደጋጋሚ ለሚገጥማቸው ብልሽትና ለሚያስፈልጋቸው ጥገና አስፈላጊ ቁሳቁስ ማሟላት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ጥቁር አንበሳ ሆስፒታልን ጨምሮ ለጅማ፣ ሃሮማያ፣ ጎንደር፣ ጳውሎስ፣ ሃይደርና ሐዋሳ አዲስ የጨረር ህክምና ማሽን እንደተገዛ ነው የተገለጸው፡፡

ዶክተር ኤዶም እንዳሉትም ለዚህ ችግር ትልቁ መፍትሄ የተገዙ የካንሰር ህክምና ማሽኖች በፍጥነት ወደ አገልግሎት እንዲገቡ ማድረግና ያሉትም ችግር እንዳይገጥማቸው ቅድሚያ አስፈላጊ ቁሳቁሶችን ማሟላት እንደሆነ ጠቅሰዋል።

በተያያዘም ህክምና ክፍሉ ለድንገተኛ ታካሚዎች ቅድሚያ የሚሰጥ እንደሆነ የገለጹት ኃላፊዋ ፥ ሌሎች ታካሚዎች ወረፋ እንዲጠብቁ እንደሚደረግም አስረድተዋል፡፡

በዚህ ምክንያት ወረፋ የሚጠብቁ ታካሚዎች ካለባቸው ጤና ችግር በተጨማሪ ሌላ የጤና እክል ይደርስብናል በሚል ያነሱትን ቅሬታም ይጋራሉ።

ይህን ችግር ለመቅረፍም የህክምና ባለሙያዎች የእረፍት ሰዓታቸውን በመጠቀምና ተመጣጣኝ ያሉትን ገንዘብ በማስከፈል ታካሚዎች አገልግሎት እንዲያገኙ እንደሚደረግም ተናግረዋል፡፡

ይህም ወረፋውን በትንሹም ቢሆን የሚያቃልል እንደሆነ ገልጸው ፥ በውጪ ሀገር ለመታከም የሚያወጡትን አላስፈላጊ ወጪ፣ ድካምና እንግልት ለማስቀረት ያስቻለ እንደሆነም ነው ዶክተር ኤዶም ያነሱት፡፡

ጣቢያችን ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጤና ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት የተገዙ ማሽነሪዎችን ወደ ስራ በፍጥነት ለማስገባት እየተደረገ ያለ ጥረት ካለ እና በአጠቃላይ ከህክምናው ጋር ተያይዞ አገልግሎቱን ለማስፋት እየተከናወነ ያለ ስራን በተመለከተ ምላሸ እንዲሰጡን በተደጋጋሚ ቢሞክርም አልተሳካም፡፡

በመሰረት አወቀ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.