በቦረና ለሚደረግ ድጋፍ በቡድንም ሆነ በተናጠል መሰብሰብ እንደማይፈቀድ የክልሉ መንግስት አሳሰበ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 2፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በቦረና ዞን በተከሰተው ድርቅ ምክንያት ድጋፍ ለማድረግ በቡድንም ሆነ በተናጠል መሰብሰብ እንደማይፈቀድ የኦሮሚያ ክልል መንግስት አሳሰበ፡፡
የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በጉዳዩ ላይ አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል፡፡
በመግለጫውም በክልሉ አንዳንድ ዞኖች በተለይም በቦረና ዞን በተከታታይ አምስት የዝናብ ወቅት ዝናብ አለመጣሉን ተከትሎ ድርቅ መከሰቱ ተጠቁሟል፡፡
በተከሰተዉ ድርቅ ምክንያትም መንግስት ባቀረበዉ ጥሪ መሠረት ለችግር ለተጋለጡ ዜጎች በተለያዩ መንገዶች በገንዘብና በዓይነት ድጋፍ እየተሰበሰበ እንደሚገኝ ይታወቃል።
ከዚህ በኋላ ከኦሮሚያ ክልል መንግስት ወይም ከኦሮሚያ ቡሳ ጎኖፋ እዉቅና ዉጭ በቡድንም ሆነ በተናጠል ድጋፍ ማድረግ የማይፈቀድ መሆኑን የክልሉ መንገስት አስታውቋል፡፡
ይህም የሚሰበሰበዉን ድጋፍ በአግባቡ ለማስተዳደር፣ ፍትሓዊ በሆነና ግልፅነት ባለዉ መንገድ ለችግር ለተጋለጡ ወገኖች ተደራሽ ለማድረግ ያለመ ውሳኔ መሆኑን በመግለጫው መጠቀሱን ኦቢኤን ዘግቧል፡፡