Fana: At a Speed of Life!

በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ከ52 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል- ግብርና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በዘንድሮ ዓመት በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ከ52 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

የግብርና ሚኒስቴር ከፍተኛ የሥራ ሀላፊዎች፣የክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊዎች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት በኦሮሚያ ክልል በምስራቅ ሸዋ ዞን በተለያዩ ወረዳዎች እየለማ ያለውን የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ጎብኝተዋል፡፡

የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ÷ ጉብኝቱ ሀገር አቀፍ የመስክ ጉብኝት መሆኑን ጠቅሰው አንዱ ክልል ከሌላው የተሻሉ ልምዶችን የሚቀስምበት፣ ተመራማሪዎችና የዩኒቨርሲቲ ምሁራኖች ደግሞ ምክራቸውን የሚለግሱበት ነው ብለዋል፡፡

በዘንድሮ ዓመት ከ1 ነጥብ 3 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ መሸፈኑም የተገለጸ ሲሆን÷ከዚህም ውስጥ ከ52 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡

ይህ ምርት ተሰብስቦ ወደ ገበያ ሲገባ እንደ ሀገር በአሁኑ ወቅት እየታየ ያለውን የገበያ አለመረጋጋት በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚፈታም ዶክተር ግርማ አመንቴ ጠቁመዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል የግብርና ቢሮ ሃላፊ ጌቱ ገመቹ በበኩላቸው÷በዘንድሮ አመት እንደ ክልል ከ1 ነጥብ 1 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ በመሸፈን ከ38 ነጥብ 5 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት እየተሰራ መሆኑን መግለፃቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.