በአዲስ አበባ ከያዝነው ወር ጀምሮ በመንግሥት መስሪያ ቤቶች የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ይጀመራል
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከመጋቢት ወር 2015 ዓ.ም ጀምሮ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተጠሪ በሆኑ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ላይ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ እንደሚጀመር የአዲስ አበባ ወሳኝ ኩነት ምዝገባ እና መረጃ ኤጀንሲ ገለጸ፡፡
በኤጀንሲው የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ዮሴፍ ንጉሴ እንደገለጹት÷ ተጠሪነታቸው ለከተማ አሥተዳደሩ በሆኑ የመንግሥት ተቋማት የሚሠሩ ሠራተኞችን በወሳኝ ኩነት ሥራው ተደራሽ ለማድረግ እየተሠራ ነው፡፡
ለዚህም ኤጀንሲው እና የአዲስ አበባ ከተማ ፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ኃብት ልማት ቢሮ በሥራው አተገባበር ላይ የየራሳቸውን ድርሻ ለይተው ተፈራመዋል ነው ያሉት፡፡
ስምምነቱም በየደረጃው ባሉ በከተማዋ የመንግስት መስርያ ቤቶች ተፈፃሚ ይደረጋል ነው ያሉት፡፡
የመንግስት ሠራተኞችም÷ ለወሊድ እረፍት የሚወጡ ወላጆች (አባት እና እናት) የልጆቻቸውን የልደት ምዝገባ ማስረጃ እንዲሁም ለጋብቻ እረፍት የሚወጡ ተጋቢዎች የጋብቻ ምዝገባ ማስረጃ እንዲያቀርቡ ይገደዳሉ ብለዋል፡፡
በተጨማሪም የቅርብ የቤተሰብ አባል ህልፈት በመከሰቱ እረፍት የሚወጡ የሞት ምዝገባ ማስረጃ እንዲያቀርቡ፣ የጉዲፈቻ እና የፍቺ ኩነት ሲከሰትም በተመሳሳይ ሁኔታ የምዝገባ ማስረጃውን ማቅረብ አስገዳጅ ነው ተብሏል፡፡
ሥራውም ከመጋቢት ወር ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግ ነው አቶ ዮሴፍ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የተናገሩት፡፡
ልደት በ90 ቀናት እንዲሁም ጋብቻ፣ ሞት፣ ፍቺ እና ጉዲፈቻን በ30 ቀናት ውስጥ ማስመዝገብ ይጠበቃል ነው ያሉት፡፡
ምዝገባው በዲጂታል እንደሚከናወን እና ለተመዝጋቢዎች የሚሰጡ የህትመት ግብዓቶችም ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡
ሠራተኞች ምዝገባውን ማከናወን ያለባቸው በሚሠሩበት መስሪያ ቤት ሳይሆን በሚኖሩበት ወረዳ መሆኑንም አስረድተዋል።
ኤጀንሲው እስካሁን በአዲስ አበባ ከሚገኙ የጤና ተቋማት፣ ዕድሮች እና ፍርድ ቤቶች ጋር የወሳኝ ኩነት ሥራውን እያከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በዮሐንስ ደርበው
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!