የጉዞ ታሪክ ያላቸው ዜጎችን በማፈላለግ ከጤና ተቋማት ጋር የማገናኘት ስራ እየተከናወነ ነው- ጤና ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 4፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የጉዞ ታሪክ ያላቸው ዜጎችን በማፈላለግ ከጤና ተቋማት ጋር የማገናኘት ስራ እየተከናወነ መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ገለፁ።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ በኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ ምላሽ አሰጣጥን በተመለከተ በማህበራዊ ትስስር ድረ ገፆች ለቀረቡላቸው ከ2 ሺህ 500 በላይ ጥያቄዎች በፌስቡክ ገፃቸው በቀጥታ ቀርበው ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ በማብራሪያቸው እንደገለፁት፥ ቫይረሱ በዓለማችን መከሰቱ ከተሰማ ጀምሮ ለመከላከል የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል።
ብሄራዊ የጤና ምላሽ ግብረ ኃይል የተቋቋመ መሆኑን ጠቅሰው በጠቅላይ ሚኒስትሩና በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመሩ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ኮሚቴዎች መቋቋማቸውንም ተናግረዋል።
በተለይም ቫይረሱን ለመግታት ቁልፉ ጉዳይ ግንዛቤ በመሆኑም ሚኒስቴሩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን የኀብረተሰቡን ግንዛቤ ማስፋት ላይ በትኩረት እየሰራ መሆኑን አንስተዋል።
በአሁኑ ወቅትም አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ክልሎች ቤት ለቤት የግንዛቤ ማስጨበጫ ተግባራት ተጀምሯል ያሉት ሚኒስትሯ ይህም በጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች እየተካሄደ መሆኑን አብራርተዋል።
እንደ ሚኒስትሯ ገለጻ፤ የጉዞ ታሪክ ያላቸው ዜጎችን በማፈላለግ ከጤና ተቋማት ጋር የማገናኘቱ ተግባርም እየተከናወነም ይገኛል።
ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎችም በተለያዩ ቋንቋዎች ተዘጋጅተው ተደራሽ እየተደረጉ ሲሆን፥ በምልክት ቋንቋም በስፋት ለማቅረብ ዝግጅቶች እየተጠናቀቁ ነው ማለታቸውን የኢዜአ ዘገባ ያመለክታል።
ክልሎች በአሁኑ ወቅት ነጻ የስልክ መስመር መክፈታቸውንም የገለፁት ሚኒስትሯ፤ ”በ8335 እና በ952 የሚሰጠውን አገልግሎት ተደራሽነት ለማስፋት ሚኒስቴሩ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር እየሰራ ነው” ሲሉም ጠቁመዋል።
ከቫይረሱ ጋር በተገናኘ የሚሰጡ መረጃዎች አውታሮችን የማስፋት ተግባራት የተከናወነ መሆኑን የገለጹት ዶክተር ሊያ፥ ዋትስአፕና በሌሎች መተግበሪያዎች መረጃዎችን ለማሰራጨት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም አመልክተዋል።
49 ማኀብረሰብ አቀፍ ሬዲዮ ጣቢያዎችን በመጠቀም ግንዛቤ ለማስጨበጥና መረጃዎችን ለማድረስ እየተሰራ እንደሆነም አክለዋል።
በበሽታው የሚያዙ ሰዎችን በተመለከተ ሚኒስትሯ ለተነሳላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ ”ህሙማንን ማግለል ተገቢ አይደለም ማህበረሰቡ አስፈላጊውን እንክብካቤ ሊያደርግላቸው ይገባል” ሲሉ አብራርተዋል።
”ነገር ግን ለጥንቃቄ ሲባል የህሙማን አድራሻ ቢገለጽ የሚሉ ጥያዎች ይነሳሉ” ያሉት ዶክተር ሊያ፥ የታካሚዎችን አድራሻና ተያያዥ መረጃዎች ይፋ ማድረግ የህክምና ሥነ ምግባር እንደማይፈቅድ አስረድተዋል።
ከህክምና ባለሙያዎች ጋር በተያያዘ ለቀረበላቸው ጥያቄም ዶክተር ሊያ፥ የህክምና ባለሙያዎች ደህንነታቸው ተጠብቆ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማስቻል የመኖሪያ ቤት፣ ስልጠና እና የመከላከያ አልባሳትን በበቂ ሁኔታ ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲያገኙም ከትራንስፖርት ሚኒስቴር ጋር በቅርበት እየተሰራ እንደሚገኝ የገለፁ ሲሆን፥ በተለይ የኮሮናቫይረስ ህሙማንን በቅርበት ለሚከታተሉ የሕክምና ባለሙያዎች ቫይረሱ ቢያዙና በዚሁ ምክንያት ሕይወታቸው ቢያልፍ የህይወት መድህን ዋስትና ለመግባት እንቅስቃሴ መጀመሩን ገልፀዋል።