Fana: At a Speed of Life!

በሕገ-ወጥ የዶላር ዝውውርና በሌሎች ወንጀሎች የተጠረጠሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ዋሉ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል በሕገ ወጥ የዶላር ዝውውርና በሌሎች ወንጀሎች የተጠረጠሩ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር አዋለ፡፡

ግብረኃይሉ÷ መጋቢት 2 ቀን 2015 ዓ.ም በአዲስ አበባ በተለያዩ አካባቢዎች ባካሄደው ኦፕሬሽን በሕገ ወጥ የዶላር ዝውውር፣ በተለያዩ ሀገራት ሐሰተኛ ገንዘቦችና በሐሰተኛ የብር ህትመት እንዲሁም በሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር የተጠረጠሩ አምስት ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እየተጣራባቸው መሆኑን አስታውቋል።

ግብረ ኃይሉ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የላከው መረጃ እንዳመላከተው÷ በተካሄደው ኦፕሬሽን ለሕገ ወጥ ዝውውር የተዘጋጀ በርካታ የአሜሪካን ዶላር እና የተለያዩ ሀገራት ገንዘቦች መያዛቸው ተገልጿል፡፡

በዚህም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በግለሰብ ደረጃ ከ100 ሺህ ብር በላይ ለድርጅቶች ከ200 ሺህ ብር በላይ በቤትና በድርጅት ውስጥ እንዳያስቀምጡ ያስተላለፈውን ክልከላ በመተላለፍ ለዶላር ግዥ ሊውል የነበረ 601 ሺህ 760 ብር፣ በሦስት ቼኮች ተፈርሞ ለሕገ ወጥ የዶላር ግዥ ሊውል የነበረ 4 ሚሊየን 900 ሺህ ብር በቁጥጥር ስር መዋሉ ነው የተገለጸው፡፡

በተጨማሪም ሦስት ክላሽንኮቭ እና አራት ሽጉጦች ከመሰል ጥይቶች ጋር በሕገ ወጥ መንገድ ይዘው የተገኙ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ውለው ምርመራ እየተጣራ ነው ተብሏል፡፡

እንዲሁም አንዳንድ የውጭ ሀገር ዜጎች የቱሪስት ቪዛና ሌሎች ህጋዊ መንገዶችን በመጠቀም ወደ ኢትዮጵያ ከገቡ በኋላ ሰወር ያሉ አካባቢዎች በሚገኙ ፔኒሲዮኖችና ሆቴሎችን ለረጅም ጊዜ በመከራየት ሐሰተኛ ዶላርና ብር በማተም የሀገራችንን ኢኮኖሚ ለማዳከም የተሰማሩ ተጠርጣሪዎች ለዶላሩና ለብሩ ማተሚያ ከሚጠቀሙባቸው ወረቀቶችና ኬሚካሎች ጋር በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራ እየተጣራባቸው እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ይህንን ሕገ ወጥ ተግባር የሚፈጽሙት አደንዛዥ ዕፅ በመጠቀም እንደሆነም በምርመራ ተደርሶበታል ነው ያለው የጋራ ግብረ ኃይሉ፡፡

የተጀመረው ኦፕሬሽን በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ እንደማይወሰን እና ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር በሚካሄድባቸው ሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገልጿል፡፡

ግብረ ኃይሉ እንደገለጸው÷ በእነዚህ አደገኛ የወንጀል ተግባራት ላይ የተሰማሩ ተጠርጣሪዎች ከነኤግዚቢቶቻቸው በቁጥጥር ሥር ሊውሉ የቻሉት በኅብረተሰቡ ጥቆማና በጋራ ግብረ ኃይሉ ጠንካራ ኦፕሬሽን ነው፡፡

ኅብረተሰቡ ላደረገው ትብብር ምስጋና ያቀረበው ግብረ ኃይሉ÷ በየትኛውም አካባቢ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ የሚፈጸሙ መሰል የወንጀል ተግባራትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ኅብረተሰቡ ከፀጥታ አካላት ጋር ተገቢውን ቅንጅት በማድረግና ጥቆማ በመስጠት እያደረገ ያለውን ቀና ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀርቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.