በኢትዮጵያና ሶማሊያ ህዝቦች መካከል ያለው ትብብር እያደገ ነው – የሶማሊያ ፕሬዚዳንት
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች መካከል ከሰላምና መረጋጋት ባለፈ በሌሎች ጉዳዮች ላይ ያለው ትብብር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ መሃሙድ ገለጹ፡፡
በሶማሊያ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሙክታር መሀመድ የሹመት ደብዳቤያቸውን ለሶማሊያው ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ መሃሙድ አቅርበዋል።
ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ መሃሙድ በዚህ ወቅት ፥ ኢትዮጵያ ለሶማሊያ ሰላምና መረጋጋት እያበረከተች ላለችው አስተዋፅዖ አመስግነዋል፡፡
አክለውም ፥ በሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች መካከል ከሰላምና መረጋጋት ባለፈ በሌሎች ጉዳዮች ላይ ያለው ትብብር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።
አምባሳደር ሙክታር መሃመድ በበኩላቸው ፥ ሶማሊያ እና ኢትዮጵያ የተለያዩ እሴቶችን እንደሚጋሩ ገልጸዋል፡፡
ሁለቱ ሀገራት በሰላምና ፀጥታ ዙሪያ ከሚያደርጉት ትብብር ባሻገር በሌሎች ዘርፎች ያለው የትብብር ልምድ ሊዳብር ይገባል ማለታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።