የኢትዮጵያውያንን ሠላም፣ አንድነትና ልማት የማረጋገጥ ጥረቶች ቻይና ገለልተኛ ሆና ትደግፋለች – የሀገሪቱ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ ሠላም፣ አንድነትና ልማት ለማረጋገጥ የሚያደርጓቸውን ጥረቶች ቻይና ገለልተኛ ሆና እንደምትደግፍ የሀገሪቱ የአፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች ልዩ መልዕክተኛ ሺየ ቢንግ ተናገሩ።
ሀገራት በሰብዓዊ መብት እና ዴሞክራሲ ሽፋን በሌሎች ሀገራት ሉዓላዊነት እና የሀገር ውስጥ ጉዳዮች ላይ የሚደያደርጉትን ጣልቃ ገብነት ቻይና አጥብቃ እንደምትቃወምም ልዩ መልዕክተኛው ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ ጉብኝት እያደረጉ የሚገኙት ሺየ ቢንግ ዛሬ በሰጡት መግለጫ፥ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የተከሰተው ግጭት የኢትዮጵያውያን የውስጥ ጉዳይ እንደሆነና በኢትዮጵያውያን ሊፈታ የሚችል መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ከጅምሩ ኢትዮጵያ “የአፍሪካን ችግር በአፍሪካውያን” ብላ መነሳቷና በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ለተከሰተው የሠላም ዕጦትም ሠላም ለመሻት የሄደችበትን መንገድ ያለ ማወላወል በራሷ መወሰኗ ኢትዮጵያውያን ልዩነታቸውን በራሳቸው በድርድርና በውይይት ለመፍታት ምን ያኅል ጥበብ እንዳላቸው ያሳየ ነው ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል በተቀናጀ ጥረት ሳዑዲ አረቢያ እና ኢራን በቤጂንግ ያደረጉት ውይይት ትልቅ ውጤት ማስገኘቱን ተናግረዋል፡፡
ሳዑዲ አረቢያ እና ኢራን ግንኙነታቸውን የሚያሻሽሉበትን ፍኖተ ካርታ እና የጊዜ ሰሌዳን ለይተው አውቀዋል፣ ይህም ትብብራቸውን ወደፊት ለመቀጠል ጠንካራ መሰረት የሚፈጥር እና በሁለትዮሽ ግንኙነታቸው ላይ አዲስ ገፅ የከፈተ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ውይይታቸውና ስምምነቱ የቀጣናው ሀገራት አለመግባባቶችን በመፍታት መልካም ጉርብትና በውይይት እና በመመካከር እንዴት መፍጠር እንደሚችሉ ጥሩ ማሳያ ነው ብለዋል።
የአፍሪካ ሀገራትን ዕዳ በተመለከተ በሰጡት አስተያየት፥ ከአለም አቀፍ ተቋማት እና ጥናቶች የተገኙ መረጃዎች እንደሚያሳዩት የአፍሪካ ሀገራት ዕዳ በዋናነት ከምዕራባውያን የግል አበዳሪዎች የተያዘ ቦንድ መሆኑን አንስተዋል።
የኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ የጂኦፖለቲካዊ ግጭቶች እና ከመጠን ያለፈ ተቋማዊ ብድር ደግም በአፍሪካ ለሚታየው የዕዳ ችግሮች ምክንያት መሆናቸውን አንስተዋል፡፡
የአሜሪካ ዶላር መጨመርም ለአፍሪካ ሀገራት የእዳ አገልግሎት ሸክም መሆኑንም ነው የገለፁት፡፡
የአሜሪካ ሃላፊነት የጎደለው የገንዘብ ፖሊሲ በግልጽ የእነዚህን ሀገራት የዕዳ ችግር እንደሚያባብሰውም ተናግረዋል፡፡
በዚህም የዓለም ባንክ እና የአይ ኤም ኤፍ ትልቅ ባለድርሻ እንደመሆናቸው መጠን ኃላፊነታቸውን ወስደው ትልቁን ሚና መጫወት እንዳለባቸውም ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ፣ ቻድ እና ዛምቢያ የዕዳ ጫናቸውን እንዲቀንሱ ለማድረግ ቻይና በቡድን 20 የዕዳ ስረዛ ኤኒሼቲቭ ላይ በንቃት መሳተፏን አንስተዋል፡፡
እንዲሁም የዕዳ ስረዛ ስምምነቶችን ተፈራርማ ከ19 የአፍሪካ ሀገራት ጋር የዕዳ ስረዛ ላይ ስምምነት ላይ መድራሷንም አንስተዋል፡፡